ሰኔ 24/2013 (ዋልታ) – በመንግሥት በኩል እየተወሰደ ያለው የታክቲክ ለውጥና የተናጠል የተኩስ አቁም የትግራይ ህዝብ በራሱ ጉዳይ ከውዥንብር ወጥቶ እንዲያስብ እድል የሚሰጥ እንደሆነ የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበርና የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ አስታወቁ።
ዶክተር አረጋዊ መንግሥት ያደረገውን የተናጠል የተኩስ አቁም አስመልክተው ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ለማድረግ የወሰነው ያየውን አይቶ፤ ማድረግ እንዳለበትም አምኖ ስለሆነ የሚያመጣው ችግር የለም፤ ከዚህ ይልቅ የትግራይ ህዝብ በራሱ ጉዳይ ከውዥንብር ወጥቶ እንዲያስብ እድል የሚሰጥ ነው።
ህዝቡ የሚያምነውና ብዙ መስዋዕትነት የከፈለለት አሸባሪው የጁንታ ቡድን አሁን እየታየ ባለው መልኩ በግልጽ ህዝቡን እየጎዳው ነው ያሉት ዶክተር አረጋዊ፣ ህዝቡ ጥቅምና ጉዳቱን ይለይ ዘንድ ትንሽ የማሰቢያ ጊዜ እንዲያገኝ መደረጉ መልካም መሆኑን አመልክተዋል።
ህዝቡ ይህንን ጊዜ ተጠቅሞ፣ አስቦና አሰላስሎ ወደራሱ ተመልሶ የሚጠቅምና የሚጎዳውን መለየት ከቻለ በመንግሥት ከተወሰደው የተናጠል የተኩስ አቁም ተጠቃሚ ይሆናል የሚል የጸና እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።