የተገነቡ ቤቶች ተጠናቀው ለተጠቃሚው መተላለፍ እንዳለባቸው ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

ኅዳር 7/2015 (ዋልታ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ፣ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአራት ሳይቶች እየተገነቡ ያሉ ቤቶች የመጨረሻ ሥራቸው ተጠናቆ ለጠቃሚዎች መተላለፍ እንዳለባቸው አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ይህን ማሳሰቢያ የሰጠው በዋናው መሥሪያ ቤትና በቅርንጫፍ ሁለት ጽሕፈት ቤት ያለው እንቅስቃሴ እንዲሁም በሦስት ቁጥር ማዞሪያ፣ በመካኒሳ፣ በቦሌ እና በገርጂ ሳይቶች የተገነቡ ቤቶችን ተዘዋውሮ ከተመለከተ በኋላ ለፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች በሰጠው ግብረ መልስ ነው ተብሏል፡፡

የከተማ፣ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሸዊት ሻንካ ኮርፖሬሽኑ በየሳይቶቹ ያስገነባቸው ቤቶች 95 በመቶ ስለተጠናቀቁ የዜጎችን ቅሬታ ለመፍታት እና የኮርፖሬሽኑን ገቢ ለማሳደግ የሚቀረውን አምስት በመቶ ሥራ በማጠናቀቅ ቤቶቹን ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የጀመራቸውን ቤቶች ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በተያዘው በጀትና ጊዜ በጥራት ማጠናቀቁን በጥንካሬ አንስተው ተቋሙ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ባለፉት አራት ዓመታት ባደረገው ሪፎርም ለሠራተኞች ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠሩ ለፕሮጀክቶቹ ሥራ መፋጠን አስተዋጽዖ እንዳለውም አብራርተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ እሸቱ ተመስገን (ዶ/ር) የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በሰራው ሪፎርም እና አሰሪው፣ የሥራ ተቋራጩና አማካሪው ተቀናጅተው መሥራታቸው የአመራሩን ቁርጠኝነት የሚያሳይ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ያለው የፕሮጀክቶች አፈፃፀም ጥሩ በመሆኑ ሌሎች አካላት እንደተሞክሮ ሊወስዱ እንደሚገባ ጠቁመው የቤቶቹ ግንባታ ተጠናቆ ለሚፈለገው ዓላማ መዋል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ የዜጎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ፍላጎት ያላቸውን ተቋማትና ክልሎችን እየደገፈ መሆኑን ጠቁመው አሰሪው፣ የሥራ ተቋራጩ እና አማካሪው በየሳምንቱ በመወያየት ችግሮቻቸውን እየፈቱ በመሄዳቸው ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜና በጀት በጥራት ሊጠናቀቁ መቻላቸውን አብራርተዋል፡፡
የቤቶቹ ግንባታ አምስት በመቶ ያልተጠናቀቀውም ከውጭ የሚመጡ ዕቃዎች በተለያዬ ምክንያት በመዘግየታቸው በመሆኑ ዕቃዎች ተገዝተው እንደመጡ የቤቶችን ግንባታ እንደሚያጠናቅቁ ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የሰጠውን አስተያየት እንደግብዓት ወስደው የሚሰሩ መሆኑን ገልፀው ኮርፖሬሽኑ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን የቋሚ ኮሚቴው ድጋፍና እገዛ እንደሚፈልጋቸው መግለፃቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡