የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመራሮች በጉራጌ ዞን የልማት ስራዎችን ጎበኙ

ጥቅምት 16/2015 (ዋልታ) በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ሱሩር የተመራው የተፎካካሪ ፓርቲዎች ስራ አስፈፃሚና አመራሮች በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

አመራሮቹ በወረዳው የሚገኙ በክላስተር የተዘሩ የስንዴ፣ ጤፍ፣ ባቄላና የበቆሎ ሰብሎችን ተመልክተዋል።

የግብርና ቢሮ ኃላፊ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት ሀገሪቱ ካለችበት ድህነት እንድትወጣ የኢኮኖሚያችን መሰረት የሆነውን ግብርና በማዘመን የዜጎችን ገቢና ኑሮ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

መንግስት ህብረተሰቡ የልማቱ ተሳታፊም ተጠቃሚም እንዲሆን በማስተባበር ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መታየታቸውንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያን የድህነት ታሪክ ለመቀየር ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያለንን ልየነት ወደ ጎን በመተው ህዝቡን ለልማት በማነሳሳት በጋራ ልንሰራ ይገባልም ሲሉም ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

የሶዶ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ደሴ አበጋዝ በኩላቸው በወረዳው ወደ 49 ሺሕ ሄክታር መሬት በሶስት ዋና ዋና ሀብቶች ላይ ሰብል የማልማት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሰባት ሺሕ ሄክታር በመስኖ በበጋ የሚለማ ሲሆን 42 ሺሕ የሚሆነው ደግሞ በበልግና በመኸር የሚሸፈን መሆኑን ዋና አስተዳደሪው ገልፀዋል።

ከ17 ሺሕ ሄክታር ስንዴ ውስጥ 80 በመቶው በኩታ ገጠም አስተራረስ ዜዴ የሚለማ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው መጠቆማቸውን ክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።

13 ሺሕ ሄክታር ጤፍ፣ 8 ሺሕ ሄክታር በቆሎ 15 ሄክታር ባቄላ እንዲሁም ሎሎች የጥራጥሬ አይነቶች እየለሙ መሆኑንም ጠቁመዋል ።

እየተከናወኑ ከሚገኙ የግብርና ስራዎች መካከል 60 በመቶው በሜካናይዝድ የአስተራረስ ዘዴ ተግባራዊ መደረጉንም ዋና አስተዳዳሪው አክለው ገልፀዋል።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንም መጠቀማቸውንም ዋና አስተዳዳሪው ጠቁመዋል።