መጋቢት 08/2013 (ዋልታ) – የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት 10ኛ አመት የምስረታ በዓል አስመልክቶ የብሄራዊ ሲምፖዚየም ውይይት ተካሂዷል፡፡
ሲምፖዚየሙ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የውሃ መስኖ እና ኤነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ እና ሌሎች የፌዴራል ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተውበታል።
የውይይት ሲምፖዚየሙን በይፋ ያስጀመሩት አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ ካላት ሃብት መካከል አንዱና ዋናው ዓባይ መሆኑን ጠቁመው፣ ሀገሪቱ ፍትሀዊ ሆና እስከሰራች ድረስ ተጠቃሚነቷን ሊነፍጋት የሚችል ሃይል የለም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ተፋሰሱን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ በጋራ የመጠቀም ፍላጎት ያላት ሲሆን፣ ፍትሃዊ አጠቃቀምን ወደ ጎን ትተው ሉዓላዊነትን የሚጋፉ በተፈጠሩበት ወቅት ውስጣዊ አንድነታችን አጠናክረን ችግሮችን መቋቋም እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በማመን የምትሰራ ሀገር መሆኗን የገለጹት የውሃ መስኖ እና ኤነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ የተፋሰሱ ተጠቃሚ ሀገራት ተመሳሳይ እና የሚያግባባ ሀሳብ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።
በትኩረት፣ በጥንቃቄ እና በመተባበር በመስራት ግድቡን ከጫፍ ለማድረስ ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባም አሳስበዋል።
(በብርሃኑ አበራ)