የታንዛኒያ ገቢዎች ኮሚሽን ልኡካን ቡድን ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር የልምድ ልውውጥ አደረጉ

ኅዳር 8/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ገቢዎች ሚኒስቴር ከታንዛኒያ የገቢዎች ባለስልጣን ልኡካን ቡድን ጋር የልምድ ልውውጥ አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያና ታንዛኒያ ከዚህ ቀደም በአቅም ግንባታና በተጨማሪ እሴት ታክስ አስተዳደርና ሌሎች ጉዳዮች የልምድ ልውውጥ ሲያደርጉ መቆየታቸውን በገቢዎች ሚኒስቴር የሚኒስትር አማካሪ ነብዩ ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ ጎረቤት ሃገራት የሚያደርጉት የጋራ የልምድ ልውውጥ በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማምጣትም ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

ቀልጣፋና ተደራሽ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የሃገሪቱን ገቢ በአስተማማኝ መልኩ ለመገንባት በዘርፉ የተሻለ ልምድ ካላት ኢትዮጵያ ጋር የልምድ ልውውጥ ማድረግ ተመራጭ ማድረጋቸውን በታንዛኒያ ገቢዎች ባለስልጣን የሰው ሃብት አስተዳደር ዳይሬክተር ሚካኤል ጆን ተናግረዋል፡፡

ልዑካኑ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከልን፣ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትንና የጉምሩክ ኮሚሽንን ተዘዋዋረው መጎብኘታቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ አመላክቷል።