የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ ማረፋቸውን ተገለጸ

የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ

መጋቢት 09/2013 (ዋልታ) – የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ በ61 ዓመታቸው ማረፋቸውን የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት አስታወቁ።

የታንዛኒያ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰን በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ቀርበው እንደተናገሩት፣ ፕሬዝዳንቱ ባጋጠማቸው የልብ ሕመም ምክንያት በዳሬ ሰላም ሆስፒታል ሲረዱ ቆይተው ሕይወታቸው አልፏል።

ማጉፉሊ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ከሕዝብ ዕይታ ርቀው የነበረ ሲሆን፣ ጤናቸውን በተመለከተ የተለያዩ አሉባልታዎች ሲሰሙ ነበር።

ባለፈው ሳምነት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ቢናገሩም ምንም የተረጋገጠ ነገር አልነበረም።

ምክትል ፕሬዝዳንቷ ሐሰን የፕሬዝዳንቱን ሞት ሲናገሩ “ዛሬ ብልሁ የታንዛኒያ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ . . .መሪያችንን ማጣታችንን ስናገር በእጅጉ እያዘንኩ ነው” ብለዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቷ አክለውም ለ14 ቀናት ብሔራዊ የሐዘን ቀናት በመላው አገሪቱ እንደሚሆን አውጀው በታንዛኒያ በሁሉም ስፍራ ሰንደቅ ዓላማዎች ዝቅ ብሎ ይውለበለባሉ ማለታቸውን ቢቢሲ አስነብቧል።