የትምህርት ሚኒስትሩ ማኅበራዊ አገልግሎት ሲሰጡ ለነበሩ ተማሪዎች እና መምህራን ምስጋና አቀረቡ

ብርሀኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)

ታኅሣሥ 4/2014 (ዋልታ) የትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ለአንድ ሳምንት በቆየው ማኅበራዊ አገልግሎት ለተሳተፉ ተማሪዎች እና መምህራን ምስጋና አቅርበዋል።

ለሀገራዊ ዘመቻው ውጤታማነት ለአንድ ሳምንት መደበኛ ትምህርት ተዘግቶ ሲሰጥ የነበረው ማኅበራዊ አገልግሎት ተጠናቋል።

ለአንድ ሳምንት በቆየው አገልግሎትም በመላው ሀገሪቱ ተማሪዎች እና መምህራን የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል በመሰብስብ፣ ደም በመለገስ፣ ድጋፍ በማሰባሰብ እና ስንቅ በማዘጋጀት ተሳትፈዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) ተማሪዎች እና መምህራን ሀገራዊ ጥሪውን በመቀበል ያደረጉት ንቁ ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው ዘመቻው ለሀገሩ እና ወገኑ የሚችለውን ለማድረግ የማይሰስት እና ኢትዮጵያን ወደፊት ለማሻገር ዝግጁ የሆነ ትውልድ መኖሩን ያሳየ ነው ብለዋል።

ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና እድገት ትምህርት ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ በትምህርት ገብታው ተመሳሳይ በሆነ ሀገራዊ ስሜትና ቁርጠኝነት ተግታችሁ እንደምትሰሩ ሙሉ እምነት አለኝ ሲሉም ተናግረዋል።

ተማሪዎችም ከዛሬ ጀምሮ መደበኛ ትምህርት መጀመራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።