የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ

መጋቢት 13/2013 (ዋልታ) – በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የሚስተዋለውን የትምህርት ጥራት ችግር ለመፍታት ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት ሊሰሩ እንደሚገባ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡
ሚኒስቴሩ በቀጣይ 10 ዓመታት የልማት መሪ እቅድ፣ ፖሊሲ እና በፖሊሲው ማስተግበሪያ ዙሪያ ለግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት ጀምሯል።
በሚኒስቴሩ የሀብት ስራ አመራር ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ይበልጣል አያሌው በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ በተለይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ሰፊ የጥራት ችግር ይስተዋላል።
በመንግስትና በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት ችግር እንደሚስተዋል ገልጸው፣ ይህንን ክፍተት ለመፍታት ሚኒስቴሩ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢዜአ ዘገባ እንዳመለከተው የ10 ዓመት የትምህርት ስልጠና እና ፖሊሲን አስመልክቶ የወጣውን እቅድ ለማስፈፀም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት ማረጋገጥ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል፡፡
በተለይ ለግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች ግንዛቤ ለመፍጠር እና የሚሻሻሉ ወይም የሚጨመሩ ጉዳዮች ካሉ እንደ ግብአት ለመውሰድ ስልጠናው መዘጋጀቱን ዶክተር ይበልጣል ተናግረዋል፡፡