የትራንስፖርት ዘርፍ ኢንቨስትመንት ጉባኤ ሊካሄድ ነው

መጋቢት 13/2013 (ዋልታ) – በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የትራንስፖርት ዘርፍ የኢንቨስትመንት ጉባኤ ከመጋቢት 15/2013 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የትራንስፖርት ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት በዚህ ጉባኤ በመንገድ ልማት፣ በመንገድ ትራንስፖርት፣ በሎጀስቲክስ፣ በባቡርና በአቪየሽን መስኮች 44 ያህል ፕሮጀክቶች የተለዩ ሲሆን መንግስት ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ መስራት በሚያስችሉ እድሎች ላይ ጥልቅ ውይይት ይደረጋል።
የግሉን ዘርፍ ለማሳተፍ የተለዩት 44 ፕጀክቶች በአብዛኛው የአዋጭነት ጥናት የተደረገላቸው ሲሆኑ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ ለውድድር ክፍት እንዲሆኑ ተደርጓልም ብለዋል።
የትራንስፖርት ዘርፍ የኢንቨስትመንት ጉባኤው ለግሉ ዘርፍ የኢንቨስትመንት ፍላጎት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡
በአለም ላይ ከሚገኙ ዋና ዋና የሎጀስቲክስና የወደብ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች 3 ያህሉ በጉባኤው እንደሚሳተፉ የተገለፀ ሲሆን 300 የሚደርሱ የዘርፉ ኢንቨስተሮች ፣ የፌደራልና አለም አቀፍ ተቋማት ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
(በደረሰ አማረ)