የትንሳኤ በዓልን ስናከብር ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላምና ደህንነት በመጸለይና የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ሊሆን ይገባል – የሃይማኖት አባቶች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣

ሚያዝያ 26/2016 (አዲስ ዋልታ) የትንሳኤ በዓልን ስናከብር ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላምና ደህንነት በመጸለይና የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ሊሆን እንደሚገባ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል እና የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስትያን ካውንስል ዋና ጸሃፊ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ ለትንሣኤ በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ በዓለ ትንሳኤ የእግዚአብሄር ፍቅር መገለጫና የተስፋችን ማሳያ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል ብለዋል።

ብፁዕነታቸው አክለውም ለእግዚአብሄር ክብርና ለሰው ልጆች ደኅንነት በአንድነት በመቆም ለተራቡት፣ ለተጠሙት፣ ለታረዙት፣ ለታመሙትና ለታሰሩትም ሁሉ ካለን ከፍለን በመስጠት ከኛ ጋራ በመንፈስና በሞራል በዓለ ትንሣኤውን ማሳለፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል፤ በበኩላቸው የትንሣኤ በዓል የክርስቶስን መነሣት ያስተማረን የምሥራች ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስትያን ካውንስል ዋና ጸሃፊ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ

የትንሳኤ በዓል ሲከበር የችግሮች ሁሉ መውጫ ቁልፍ ሰላም ብቻ በመሆኑ በትንሣኤው ብርሃን ለሀገርና ለህዝብ የሰላም መሣሪያ በመሆንና ለሰላም በመፀለይ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስትያን ካውንስል ዋና ጸሃፊ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ፤ ምዕመኑ የትንሳኤን በዓል ሲያከብር ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች በማገዝ ሊሆን እንደሚገባና በክርስቶስ ትንሳኤ ሁሉም በፍቅር ልብና በይቅርታ ለሰላምና አብሮነት በመጸለይ በዓሉን እንዲያከበርም መልክት ማስተላለለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።