የትዊተር ዘመቻው ምዕራባውያን ኢትዮጵያ ላይ የያዙትን የተዛባ አቋም እንዲፈትሹ እያስገደዳቸው እንደሚገኝ ተገለፀ

ነሃሴ 18/2013(ዋልታ) – አሸባሪውን ህወሓት በዕርዳታ ስም የሚደግፉ ተቋማትና ግለሰቦችን የሚቃወመው የትዊተር ዘመቻ አንዳንድ ምዕራባውያን አገሮችና ድርጅቶች በኢትዮጵያ ላይ የያዙትን የተዛባ አቋም እንዲፈትሹ እያስገደዳቸው መሆኑ ተገለጸ ። ዘመቻውም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ተገልጿል፡፡

በአባይ ጉዳይ ጸሐፊ፣ ጋዜጠኛ እና የትዊተር ዘመቻው ተሳታፊ እስሌማን አባይ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፀው፣ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያውያን ወዳጆች በእርዳታ ሰበብ የአሸባሪውን ህወሓት ወንጀል ለመደገፍ የሚንቀሳቀሱ የውጭ ተቋማት ድርጊት በመቃወም የትዊተር ዘመቻዎች እያካሄዱ ነው፡፡

በዚህም ከፍተኛ ተፅእኖ መፍጠርና የኢትዮጵያን ድምፅ ለዓለም የማሰማትና ዓለምአቀፍ ተደማጭነት የማግኘት አቅም እየተፈጠረ መምጣቱን ያመለከተው እስሌማን አባይ፣ ከቀናት በፊት ‹‹@DrTedrosResign›› በሚለው በአንድ ምሽት ዘመቻ ብቻ ከ144 ሺ በላይ ትዊት ተደርጓል፡፡ ‹‹TplfTerroristGroup›› የሚልም በሳምንቱ ከ375 ሺህ በላይ ትዊት መደረጉን አስታውቋል። በዘመቻውም 3ነ ጥብ 8 ቢሊዮን በላይ ተደራሽ መሆን መቻሉን ጠቁሟል ።

‹‹በሌሎችም መልዕክቶች በአሸባሪው ቡድን ላይ ከፍተኛ ብልጫ እያስመዘገብን እንገናኛለን ››ያለው እስሌማን፣ አሸባሪውን ህወሓት በዕርዳታ ስም የሚደግፉ ተቋማትና ግለሰቦችን የሚቃወም የትዊተር ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠሉ አንዳንድ ምዕራባውያን አገሮችና ድርጅቶች በኢትዮጵያ ላይ የያዙትን የተዛባ አቋም እንዲፈትሹ እያስገደዳቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ ተደማጭነት እየጨመረ መምጣቱን ያመላከተው እስሌማን፣›› ከቀናት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አይወግንም። በአራቱ መርሆቻችን ሰብዓዊነት፣ ገለልተኝነት፣ አለማዳላትና ራስን የቻለ በሆነ መንገድ ሰብዓዊ ተግባር እየሰራን ነው፣ በዚህ መንገድ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ያለምንም አድሎ የምናደርገውን እርዳታ የምንቀጥል ይሆናል ሲል ያወጣው መግለጫ የዚሁ እውነታ አንዱ ማሳያ ነው››ብላል፡፡

ቅዳሜ ምሽት ጀምሮ የተደረገው የትዊተር ዘመቻ‹‹StopWeaponizingAid የሚል ዋነኛ አጀንዳ የተቀረፀለት፣በቀጥታ የሳማንታ ፓወርን ቢሮን የሚመለከትና ከ 631 ሚሊዮን በላይ ተደራሽ ያገኘው እንደነበር ያስታወሰው ጋዜጠኛ እስሌማን፣ በቀጣዩ ቀን ሳማንታ ፓወር ‹‹የህወሓት ትንኮሳ ኢትዮጵያን ከመጉዳት ያለፈ ትርፍ አያመጣም›› የሚል መልእት ማጋራታችንም ዘመቻው ተፅእኖ እያመጣ ስለመምጣቱ ሌላው ማሳያ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

‹‹ጥንቃቄው፣ ጥርጣሬው የዲፕሎማሲ ብልሃትና ትግሉ መቀጠል እንዳለበት ሳንዘነጋ የሴትዮዋ የአቋም ለውጥ በጦር ሜዳውና በዲጂታሉ ፍልሚያዎቹ የተገኙ ድሎችን ተከትሎ የተፈጠረ ስለመሆኑ አጠራጣሪ አይሆንም›› ማለቱን ኢፕድ ዘግቧል፡፡

ምዕራባውያን ኢትዮጵያ ላይ የያዙትን የተዛባ አቋም እንዲፈትሹና እንዲያስተካክሉ የሚጠይቀው የትዊተር ዘመቻው ለውጥ እያመጣ በመሆኑ ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጿል፡፡አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን አሸባሪውን ህወሓት በዕርዳታ ስም የሚደግፉ ተቋማትና ግለሰቦችን የሚቃወሙ የትዊተር ዘመቻዎችን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡