ነሀሴ 20/2013 (ዋልታ) – አንዳንድ የትግራይ ዳያስፖራ አባላት “ራሳቸው የተደላዳለ ሕይወት እየኖሩ የትግራይ ሕዝብ ከስቃይና መከራ እንዳይወጣ ሲሰሩ ማየት ያሳዝናል” ሲሉ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ እስፈጻሚ ተናገሩ፡፡
ዶክተር አብርሃም አሸባሪው ሕወሓት ላለፉት 50 ዓመታት ስሙን ከትግራይ ሕዝብ ጋር አቆራኝቶ ቢጠቀምም “አንድም ቀን አጀንዳውን የትግራይ ህዝብ አድርጎት አያውቅም” ብለዋል፡፡
ይልቁንም የትግራይ ሕዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ የአሻባሪው ሕወሓት ሴራና ክፋት ሰለባ ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
አንዳንዱ ዲያስፖራ በተሻለ አገር የተደላዳለ ኑሮ እየመራ የትግራይ ሕዝብ ስቃይ ማብቂያ እንዳይኖረው የሽብር ቡድኑን እያገዘ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
“ሕዝብ በየደቂቃው እየታረደ፣ ሕጻናት እየረገፉ ምንም የማይመስላቸው የትግራይ ተወላጆች እጅግ የሚያሳዝን ተግባር እየፈጸሙ ነው” ብለዋል።
የትግራይ ሕዝብ ስለ አሸባሪው ሕወሓት የተንኮል ገመና በግልፅ እንዲረዳ ተባብሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ሰጠውታል፡፡
ይህ ከሆነ የትግራይ ሕዝብ አሸባሪውን ከራሱ ላይ ነቅሎ ለመጣል ወደ ኋላ የማይል ሕዝብ እንደሆነ በተግባር የተረጋገጠ ነው በማለት ዶክተር አብረሃም ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
”በተለያየ መልኩ በሽብር ቡድኑ ኔት ወርክ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ካሉ እነሱን ማጋለጥ ያስፈልጋል፤ ከሃዲ የትም ሊገኝ ስለሚችል” ብለዋል።
ዶክተር አብረሃም የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም ቢሆን “መሬት ላይ ያለውን እውነታ ከመቀበል ይልቅ ድብቅ ፍላጎቱን ለማሟላት እየሰራ ይገኛል” ብለዋል፡፡