ነሃሴ 08/2013 (ዋልታ) – የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት በመቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጠ።
ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ከትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ
ምድረ ቀደምቷ ሃገራችን ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ታሪክ፤ የብዙ ብሔር ብሔር ሰቦችና ቋንቋዎች ባለቤት፤ የአይበገሬዎቹ ጀግኖች ሃገር፤ የልበ ሩህሩሆች እና ቀና ልብ አባቶችና እናቶች ሃገር፤ የሰው ዘር መገኛ፤ እንግዳ ተቀባይ፤ ከማንም በላይ ሰብአዊነትና ስብእና የሚያስቀድም ህዝብ፤ ለፈጣሪ እንጂ ለማንም የማትንበረከክ እናት ሃገራችን፤ በጣም ብዙ ፈተናዎች አልፋ የውጭና የውስጥ ጠላቶችዋን ድል አድርጋ በታሪክ ላይ ታሪክ እየደራረበች እዚህ ደርሳለች፡፡
እነዚህን ፈተናዎች ስታልፍ ከማንም በላይ አንድነትዋን አጠናክራ፤ በውስጥም በውጭም የሚፈጠሩ ባንዳዎችንና ሴራቸው እያከሸፈች ታላቅነትዋ ማስጠበቅ ችሏል፡፡
አሁንም ሃገራችን ኢትዮጵያ ባንዳዎች ከውጭ ሃይሎች ጋር በጋራ በመሆን የግል ጥቅማቸው ለማስጠበቅና የሀገሪቱ ጥቅም ለውጭ ሃይሎች አሳልፈው ለመስጠት እና ከሁሉም በላይ ሆዳቸውን በማስቀደም፣ ሃገራችንን ለመበታተን፣ ህዝባችን ለመከፋፋል ቆርጠው ተነስተዋል፡፡
የዚህ ሴራ ጠንሳሽና የነፍስ አባት ደግሞ አሸባሪው የህወሃት ጥቂት የጥፋት ቡድን ነው፡፡
የጥፋት ቡድኑ ሃገራዊ ለውጡ አልቀበል ብሎ ከሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር ተነጥሎ ወደ መቀሌ ከፈረጠጠ በኋላ፤ በየቦታው ካስቀመጣቸው ተላላኪዎቹ ጋር በመሆን፤ ዜጎችን በማፈናቀል፤ ብሔር ከብሔር ጋር በማጋጨት፤ በየቦታው ሽብር በመፍጠር፤ መንግስትን እና ህዝብን ለመነጠል በሞሞከር፤ ከውጭ እና ከውስጥ ሃይሎች ጋር ሴራ በማሴር፤ ዓለም ያደነቃቸው የመንግስት ስራዎች እና ውሳኔዎች ማጠልሸት እና ማናናቅ፤ተደጋጋሚ የውሸት ፕሮፖጋንዳ በመስራት፤ ብሎም የትግራይ ህዝብን ጨቁኖ በመያዝ የጨረቃ ምርጫ ማካሄድ፤ በስተመጨረሻም በጀግናው የሃገር መከላከያ ሰራዊታችን ጭካኔ የተሞላው ክህደት በመፈጸም፤የትግራይ ህዝብ፤ልማት፤ ሰላምና አንድነት በሚሻበት ወቅት፤ህዝቡ እንዳይረጋጋ፤ ክልሉ የጦርነት አውድማ አድርገውታል፡፡
የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት የህወሃት ሴራና ሃገር የመበታተን አጀንዳ በመቃወም የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡
1. ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው ብሎ የጥፋት ሃይሉ የሚያሠራጨው ትርክት በምንም ዓይነት መንገድ ተቀባይነት የሌለው የሓሰት ዲስኩር ነው፤ፓርቲ እና ህዝብ አንድ ሆነው አያውቁም፤አንድም ሊሆኑ አይችሉም ይህ የውሸት ፕሮፖጋንዳ እናወግዛለን፡፡
2. ትግራይ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል የሚደረገው ሴራ እናወግዛለን፡፡
3. በሽብር ቡድኑ የሚደረገው ዘመቻ ፀረ-ትግራይ ህዝብ ነው እየተባለ የሚቀርበው ፕሮፖጋንዳ ተቀባይነት የሌለው እና ዘመቻው ህዝብን ምሽግ አድርጎ ህዝብ እያሥጨረሰ ካለ ሃይል፤ ህፃናትን ወደ ጦርነት ከሚማግድ ሽብር ቡድን ጋር መሆኑ እንገልፃለን፡፡
4. የጥፋት ቡድኑ የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ወንድም ህዝቡ ጋር እንዳይገናኝ፤ አርሶ እንዳይበላ፤ ሰርቶ እንዳይበላ፤ ነግዶ እንዳይገባ፤ በጨለማላይ እንዲኖር፤ ጦርነት ብቻ እንዲያሥብ ፤ ልማት እና ብልፅግና እንዲረሳ፤ ህዝብ ከህዝብ ጋር እንዲቃረን ያደረገበት አግባብ አጥብቀን እናወግዛለን፡፡
5. ራሱን ንፁህ አድርጎ መንግስትን ጥፋተኛ ለማስመሰል ከባእድ ሀገራት ጋር የሚያደርገው የሃገር ክህደት ግንኙነት እናወግዛለን፡፡
6. በአፋር ወንድም/ እህት ህዝባችን ላይ የፈፀመው ጭፍጨፋ እና ማፈናቀል እናወግዛለን፡፡
7. በአማራ ክልል ወንድም/እህት ህዝባችን ላይ የሚፈፅመው ጭፍጨፋ እና ማፈናቀል እናወግዛለን፡፡
8. በግዝያዊ አስተዳደሩ የነበሩ አመራሮች ላይ የፈፀመው፤ዘግናኝ ግድያ፤አካል ማጉደል እና ንብረት ማውደም እናወግዛለን፡፡
9. በትግራይ ያሉት የግዝያዊ አስተዳደሩ ቤተሰቦች እና ዘመዶች የሚደረግ ማሸማቀቅ፤ዘለፋ እና ትንኮሳ እናወግዛለን፡፡
10. ከትግራይ ክልል ውጭ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጅ ወገኖቻችን፤እንደ ማንኛውም ዜጋ በሰላም እና በደህንነት ወጥተው እንዲገቡ፤ሰርተው እንዲበለፅጉ ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን እንሰራለን።
11. በገንዘብ፤በሞራል፤በፕሮፖጋንዳ እና በመሳሰሉት የሽብር ሃይሉ የሚደግፉ ማናቸውም አካል እናወግዛለን፤ በህግ እንዲጠየቁም ከሚመለከተው አካል በጋራ በመሆን እንሰራለን፡፡
12. በስህተት፣ በጥርጣሬ፣ ሳይጣራና ሳይረጋገጥ የታሰሩ፣ ንብረታቸው የታገደና ንግድ ቤታቸው የተዘጋ ተጋሩ ካሉ፣ ቶሎ ፍትህ እንዲያገኙ ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን እንሰራለን፡፡
13. ማንኛውም በሃገራችን የሚደረግ የውጭ ጫና እና ጣልቃ ገብነት በፅኑ እናወግዛለን፡፡
14. ጀግናው የሃገር መከላከያ ሰራዊታችን ለሚፈፅመው የህልውና ዘመቻ የሚደረግ ማናቸውም ዓይነት ድጋፍ እና እገዛ እናደርጋለን፡፡
15. በሁሉም ክፍላተ-ዓለማት የምትገኙ አንዳንድ ተጋሩ ዲያስፖራዎች ለሽብር ቡድኑ የምታደርጉትን ድጋፍ ትታችሁ፣ ለሃገራችሁ እና ለህዝባችሁ ዘብ እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋን።
በመጨረሻም የትግራይ ህዝብ ፍላጎት ሰላምና ሃገራዊ አንድነት እዲረጋገጥ እንጂ ሃገር የማፈራረስ አጀንዳ ኖሮት አያውቅም፤አሁንም የለዉም፤ስለሆነም እየተደረገ ያለው ሃገር የመበታተን አጀንዳ የሽብር ቡድኑ ፍላጎት እና እንቅስቃሴ እንጂ ህዝባችንን አይገልፅም፡፡
ተጋሩ ለዚህ የሽብር ቡድን እንቅስቃሴ አንድ በመሆን በያለንበት ልናወግዘው ይገባል፡፡ አንድነታችን ለማረጋገጥ የምንችለውን ሁሉ ከፌዴራል መንግስት ጎን በመሆን እንድንቀሳቀስ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የትግራይ ህዝብ ወደ ብርሃን ይሸጋገራል!!
ኢትዮጵያ እጆችዋ ወደ ፈጣሪ ትዘረጋለች!
የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት
ነሓሴ 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ኢትዮጵያ