የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ በኢትዮጵያ የሚፈታ ውስጣዊ ጉዳይ ነው – የደቡብ ሱዳን ም/ፕሬዝዳንት

ነሃሴ 18/2013 (ዋልታ) –የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ሁሴን አብደል ባጊ በትግራይ የሚስተዋለው ችግር የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ በኢትዮጵያውያን ብቻ የሚፈታ መሆኑን ገለጹ።

በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች እና በደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት አፈፃፀም ዙሪያ ከሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሁሴን አብደል ባጊ ጋር ተወያይተዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንት ሁሴን አብደል ባጊ በበኩላቸው የትግራይ ሁኔታ በኢትዮጵያውያን ብቻ የሚፈታ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ስለሆነ ሀገራቸው በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ማንኛውንም የውጭ ጣልቃ ገብነት ታወግዛለች ነው ያሉት፡፡

አምባሳደር ነቢል የጋራ የልማት ፕሮጀክቶችን በመተግበር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጥልቅና የቆየ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

በተለይ በኃይል አቅርቦት እና በመንገድ መሠረተ ልማት ላይ ሁለቱ ሀገራትን ለማገናኘት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችም ሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል።

በደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ትግበራን በተመለከተ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የታዩ ማነቆዎችን ለመቅረፍ የኢትዮጵያ እገዛም ቀጣይነት ኖረዋል ነው ያሉት።

አምባሳደሩ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር እና እየተከናወነ ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ለምክትል ፕሬዝዳንቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ሁሴን አብደል ባጊ በበኩላቸው የኢትዮጵያን ህዝቦች ለነፃነታቸው እና ለሀገራቸው ሉዓላዊነት እየከፈሉ ያለውን መስዋዕትነት አድንቀዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን መካከል ያለው የረጅም ጊዜ ትስስር ከሁለትዮሽ ግንኙነት በላይ መሆኑን ገልጸው፣ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ትልቅ አክብሮት አለው ብለዋል።

ሁለቱ ሀገራት በመሰረተ ልማት መገናኘታቸው አስፈላጊ በመሆኑ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለሁለት ሱዳን ህዝቦች እና ለአጎራባች ሀገራት የጋራ ሀብት ነው ብለዋል።