የቻይና ኩባንያዎች ሴት የሥራ አመልካቾችን የእርግዝና ምርመራ በማስደረጋቸው ተከሰሱ

ሐምሌ 11/2016 (አዲስ ዋልታ) ከ12 በላይ የሚሆኑ የቻይና ኩባንያዎች ሴት የስራ አመልካቾችን የእርግዝና ምርመራ በማስደረጋቸው ክስ ተመሰረተባቸው፡፡

በምስራቃዊ የጂያንግሱ ግዛት ውስጥ በናንቶንግ የሚገኘው የቶንግዙ አውራጃ አቃቤ ህግ ቢሮ ከህዝብ በደረሰው ጥቆማ መሰረት በጉዳዩ ላይ ምርመራ በመጀመር በሁለት የህዝብ ሆስፒታሎች እና የህክምና ምርመራ ማዕከል ላይ ጥናት አድርጓል።

በዚህም በ16 የተለያዩ ኩባንያዎች ውስጥ ስራ የሚሹ 168 ሴቶች የእርግዝና ምርመራ እንደ ቅድመ-ቅጥር የጤና ምርመራ ማድረጋቸውን አረጋግጠዋል።

እንዲት የስራ አመልካች ሴት እርጉዝ በመሆኗ ምክንያት የስራ ቅጥር እንዳልተፈጸመላትም ተገልጿል፡፡

ይህንን ተከትሎ አቃቤ ህግ በድርጅቶቹ ላይ ይፋዊ ክስ መስርቶ “ድርጊቱ የሴቶችን እኩል የስራ እድል የጣሰ ነው” ብሏል።

የቻይና ህግ ቀጣሪዎች የቅድመ-ቅጥር ፈተና በሚያደርጉበት ውቅት የእርግዝና ምርመራ እንዳያደርጉ በግልፅ የሚከለክል ሲሆን አንዳንድ ኩባንያዎች የወሊድ ፈቃድ እና ጥቅማጥቅሞች ስለሚያስጨንቃቸው የሚቀጥሯቸው ሴቶች እርጉዝ አለመሆናቸውን ቀድመው ያረጋግጣሉ ነው የተባለው፡፡

ምርመራ ላይ ከነበሩት 16 ኩባንያዎች ውስጥ አራቱ ጥሰቶቹን እንዲያርሙ በይፋ የታዘዙ ሲሆን ከጉዳዩ ጋር የተገናኙት ሦስቱ የህክምና ተቋማት ደግሞ የእርግዝና ምርመራን ከቅጥር በፊት የጤና ምርመራ ላይ እንዳያካትቱ መመሪያ እንደተሰጣቸው የደቡብ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት ዘግቧል።

በቻይና ህግ መሰረት የስርዓተ-ፆታ እኩልነት ደንቦችን የሚጥሱ ኩባንያዎች እስከ 50 ሺሕ ዩዋን ወይም 6 ሺሕ 900 ዶላር ቅጣት ይጣልባቸዋል፡፡