የነዳጅ አውቶሞቢሎች እና ከፀጥታና ከደህንነት ዕቃዎች ውጪ ሌሎች ዕቃዎች ያለ ውጭ ምንዛሬ ክፍያ ወደ አገር እንዲገቡ ተፈቀደ

ነሐሴ 13/2016 (አዲስ ዋልታ) ወደ አገር እንዳይገቡ በሕግ ክልከላ ከተደረገባቸው ዕቃዎች የነዳጅ አውቶሞቢሎች እና ከፀጥታና ከደህንነት ዕቃዎች ውጪ ሌሎች ዕቃዎች ያለ ውጭ ምንዛሬ ክፍያ ወደ አገር እንዲገቡ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

መንግሥት በቅርቡ ተግባራዊ ባደረገው የተሟላ የኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ምንዛሬ በገበያው አማካኝነት እንዲወሰን ማድረጉ እና ይኸው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተግባራዊ መደረጉ ይታወቃል፡፡

ይህንኑ አስመልክቶ ገንዘብ ሚኒስቴር ያለ ውጭ ምንዛሬ ክፍያ (በፍራንኮ ቫሉታ) ዕቃዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትን በተመለከተ ለጉምሩክ ኮሚሽንና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በተላለፈ ሰርኩላር ደብዳቤ አስታውቋል።

ውሳኔው በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የገቢ ንግዱን ይበልጥ እንዲያሳልጥ እንደሚያደርገው ከሚኒስቴሩ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።፡