የአማራ ክልል መንግሥት በቄለም ወለጋ በሚኖሩ ንጹሃን ዜጎች ላይ በደረሰው ጭፍጨፋ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገለጸ

ሰኔ 28/2014 (ዋልታ) የአማራ ክልል መንግሥት በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ውስጥ በሚኖሩ ንጹሃን ዜጎች ላይ በደረሰው ጭፍጨፋ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገለጸ።

የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ግዛቸው ሙሉነህ በሰጡት መግለጫ አሸባሪው የሸኔ ቡድን ዛሬም ሰላምን በሚሻው ንጹሃን ሕዝብ ላይ የሞት ጽዋን የሚያዘንብ የጥፋት መልአክ ሆኗል ብለዋል።

የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ወገኖች ሰላምን በማይሹ የሀገርና የሕዝብ ጠላቶች እንዲህ የመጠቃታቸው ብቸኛው ግብ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማንበርከክ አልመው መሆኑን ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ውስጥ በሚኖሩ ንጹሃን ዜጎች ላይ በደረሰው ጭፍጨፋ ለመላው ሕዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል።

ዛሬም ሆነ ነገ የዚህ ችግር ብቸኛው መፍትሔ የሕዝባዊ አንድነት ጠላት እና በጋራ ሰርቶ የማደግ ደመኛ የሆኑ ፀረ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሆኑ ሁሉንም ኃይላት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንደ ሕዝብ በአንድነት ታግሎ ማሸነፍ ሲቻል ብቻ መሆኑን አመላክተዋል።

ይህን መሰል ጥቃቶችን በመፈጸም መሪር ሀዘን ላይ የሚጥሉ ጠላቶቻች ታግሎ ለማሸነፍና ለዚህ ጉዳይ ከሥሩ መፍትሔ ለመፈለግ ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድ ድምጽ ይህን ድርጊት በመቃወም የመፍትሔው አካል ሊሆን ይገባል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡