የአማራ ክልል መንግስት ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ የቀድሞ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች እየተመዘገቡ መሆኑ ተገለጸ

ሐምሌ 07/2013 (ዋልታ) – የቀድሞ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን ጨምሮ በመደበኛ ሰራዊትነት ሲያገለግሉ የነበሩ ለውጊያው ብቁ ቁመና ያላቸው የክልሉ ተወላጆች የአሸባሪውን ትህነግ ቡድን ለመመከት ምዝገባ መጀመራቸውን የአማራ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ  እንደገለጹት፤ አሸባሪው ህወሃት በስልጣን ዘመን በነበረበት ጊዜ ምንም ጉድለት ሳይኖርባቸው በመሰሪ አካሄዱ በተለያየ ሰበብ የተሰናበቱ የጦር መኮንኖች ከክልል መንግስት የቀረበው ጥሪ ተቀብለው እየተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡

በተለያየ የጸጥታ መዋቅር ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች ሲያገለግሉ የቆዩና በሀላፊነት ላይ የነበሩ አሁን ላለው ውጊያ መታገል የሚያስችል ቁመና ያላቸው የክልሉ ተወላጆች በፍቃዳቸው ምዝገባ ጀምረዋል፡፡

በተለያዩ ክልሎችና በአዲስ አበባ የሚገኙ ጥሪ የተደረገላቸው ወገኖች በተላለፈው ጥሪ መሰረት እየተመዘገቡ ናቸው፡፡ በየአካባቢውም ተሳታፊ የመሆን ከፍተኛ ፍላጎት አለ ያሉት አቶ ግዛቸው፤ ጥሪ ከመተላለፉ በፊትም ቀደም ሲል ሁኔታውን ስለሚገነዘቡ እንሳተፍ የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበርና መንግስትም ይህንን በመገንዘብ በመፍቀዱ የበለጠ ስራውን እያቀላጠፈው መሆኑን አስታውቀዋል።

በቀጣዩቹ ሶስትና አራት ቀናት ምዝገባውን በማጠናቀቅ ስልጠና ተሰጥቶ በቀጥታ ትግሉን ይቀላቀላሉ ሲለም ነው የገለጹት፡፡

ክልሉ በትህነግ የሽብር ቡድን በተከፈተበት ይፋዊ ጦርነት ከመከላከል ወጥቶ ወደ ማጥቃት መሸጋገር መጀመሩንም አቶ ግዛቸው መግለጻቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡