የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰኔ 15 ጥቃት ተጠርጣሪዎች ላይ ብይን ሰጠ

የሰኔ 15 ጥቃት ተጠርጣሪዎች

የካቲት 3/2014 (ዋልታ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰኔ 15ቱ ጥቃት ተጠርጣሪዎች ላይ ብይን ሰጥቷል፡፡

ሰኔ 15/2011 ዓ.ም በክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና የጸጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል በሚል ወንጀል ተጠርጥረው በሕግ ጥላ ስር ያሉ ተከሳሾች የፍርድ ሂደታቸው ሲታይ ቆይቷል፡፡

እስካሁን በነበረው የፍርድ ሂደት 20 ተጠርጣሪዎች በነጻ ሲለቀቁ፣ ሦስት ተጠርጣሪዎች ደግሞ በሌሉበት ጥፋተኛ ተብለው ነበር፡፡

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዛሬው የችሎት ውሎም በ32 ተጠርጣሪዎች ላይ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል፡፡

በፍርድ ሂደቱ ዐቃቤ ሕግ 76 የሰው፣ የሰነድ፣ የድምጽ እና ምስል ምስክሮች መቅረባቸውን ያወሳው ፍርድ ቤቱ ተከሳሾችም የመከላከያ ምስክሮችን እና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርበው ሲከራከሩ መቆየቱን ነው የገለጸው፡፡

በክስ መዝገቡ ከቀረቡት ተከሳሾች መካከል አራት ተከሳሾችን በነጻ አሰናብቶ በ28ቱ ላይ የጥፋተኝነት ብይን ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተከራካሪ ወገኖችን የጥፋት አስተያየት ለመቀበልም ለየካቲት 07/2014 ዓ.ም ቀጠሮ መስጠቱን የአሚኮ ዘገባ ያመለክታል፡፡