የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የገና እና የጥምቀት በዓላት ያለፀጥታ ስጋት እንዲከበሩ በቂ ዝጅት ማድረጉን ገለፀ

ታኅሣሥ 28/2014 (ዋልታ) የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የገና እና የጥምቀት በዓላት ያለፀጥታ ስጋት እንዲከበሩ በቂ ዝጅት ማድረጉን ኮሚሽነሩ ተኮላ አይፎክሩ አስታወቁ፡፡
ኮሚሽነር ተኮላ አሸባሪው ትሕነግ ወርሯቸው ከነበሩ አካባቢዎች አንዱ በነበረው ላሊበላ ከተማ የሚከበረው የልደት በዓል ያለምንም የጸጥታ ስጋት እንዲጠናቀቅ ከሌሎች የጸጥታ እና የደኅንነት ተቋማት ጋር በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት እና ጥምቀት በዓላት ያለምንም የሰላም እና የደኅንነት ስጋቶች እንዲከበሩ ግልጽ፣ ስውር፣ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ጥበቃዎች መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል፡፡
መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ፣ ፋኖ እና የፌደራል የጸጥታ ኃይሎች የእቅዱ ፈጻሚ ባለቤቶች ናቸው መባሉን አሚኮ ዘግቧል፡፡
በየአካባቢው የተጠናከረ የተቋማት ጥበቃ እና የ24 ሰዓታት የጸጥታ ፍተሻ ስለሚኖር ዜጎች በፈለጉት ጊዜ እና ቦታ ያለስጋት መንቀሳቀስ የሚችሉበት እድል ተፈጥሯልም ብለዋል፡፡