የአማራ ፋኖ ሸዋ ዕዝ ዋና አዛዥ ኮሎኔል አሰግድ መኮንን ለመንግስት ጸጥታ ኃይሎች እጁን ሰጠ


ሐምሌ 15/2016 (አዲስ ዋልታ) በአማራ ክልል በርካታ የታጣቂ ቡድን አባላት እና አመራሮች በመንግስት የቀረበላቸውን የሰላም አማራጭ ተቀብለው ሰላማዊ ሕይወት እየመሩ መሆኑን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡

የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል እንዳስታወቀው በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩትን የፀጥታ ችግሮች በንግግርና በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በመንግስት ለታጣቂ ቡድን አባላት እና አመራሮች በተደጋጋሚ የሰላም አማራጮች ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡

ይሁንና በክልሎችም ሆነ በፌደራል መንግስት እያቀረበ ያለው የሰላም አማራጭ እንዳይሳካ እና ወደ መሬት እንዳይወርድ በተለይም ደግሞ ውጭ ሆነው በትግሉ ስም ጥቅም የሚያግበሰብሱ አንዳንድ ጽንፈኛ የዳያስፖራ አባላት ሰብስበው በሚልኩት ረብጣ ዶላር እንዲሁም ንፁሃንን አግተውና በጭካኔ ገድለው በሚጠይቁት እና በሚዘርፉት ገንዘብ ጥቅም የሰከሩ አንዳንድ የታጣቂ ቡድን አባላትና አመራሮች የሰላሙን አማራጭ ሲገፉ መቆየታቸውን አመልክቷል፡፡

መግለጫው አያይዞም ከጥቅም፣ ከጎጠኝነት እና ከገንዘብ ክፍፍል ጋር በተያያዘ በአብዛኛው በታጣቂ ቡድኑ አባላት እና በቡድኑ አመራሮች መካከል በሚፈጠር አተካራ እና የእረስ በርስ መጠፋፋት የትግሉ ዓላማ ከመስመር ወጥቷል በሚል በራሳቸው በቡድኑ አባላት እና አመራሮችም ጭምር እየታየ እና እየተገለፀ መምጣቱ ክልሎችን ለግጭትና ለትርምስ እያደረገ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

ይህን ተከትሎም ለመንግሰት እጃቸውን በመስጠት ወደ ሰላማዊ ህይወት እየተቀላቀሉ ያሉ የታጣቂ ቡድን አባላት እና አመራሮች ቁጥር ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጿል፡፡

በዛሬው እለትም በአማራ ክልል የአማራ ፋኖ ሸዋ ዕዝ ዋና አዛዥ ኮሎኔል አሰግድ መኮንን ለመንግስት ፀጥታ ኃይሎች እጁን መስጠቱን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል አስታውቋል፡፡

ግለሰቡ እጁን የሰጠው በፅንፈኛ ኃይሉ አመራሮች እና ታጣቂ ቡድን አባላት አማካኝነት በአማራ ክልል ህዝብ ላይ የሚፈፀሙ አሰቃቂ ግድያዎች፣ እገታዎች፣ አስገድዶ መድፈሮች፣ ለሕዝብ ጠቀሜታ የሚውሉ መሰረት ልማቶች ውድመት፣ አፈና እና ሌሎችም ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች እየተበራከቱ በመምጣታቸው እንደሆነ በሰጠው ቃል ማረጋገጡን መግለጫው ጠቁሟል፡፡

የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አክሎም ኮሎኔል አሰግድ መኮንን እጁን የሰጠው ከቅርብ አጃቢው ገበየሁ ወንድማገኝ ከተባለ የቡድኑ አባል ጋር መሆኑን ጠቅሷል፡፡

ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመቀላቀላቸው ትግሉ በአማራ ክልል ህዝብ ስም ቢካሄድም የጠራ ጥያቄ የሌለውና ክልሉን ለምስቅልቅል እና ለልማት እጦት እያደረገ ያለ እንዲሁም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ባሉ የተለያዩ ኃይሎች ፍላጎት ማስፈፀሚያ በመጠለፉ ምክንያት እንደሆነ መግለፃቸውን በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

የጽንፈኛ ኃይሉን በሚመሩት በእስክንድር ነጋና በዘመነ ካሴ መካከል የተፈጠረው ሽኩቻ ህዝቡን የከፋ ዋጋ ከማስከፈል የዘለለ ወደ አንድ የሚመጣበት ዕድል ሊኖረው እንደማይችል መረዳቱንም ኮለኔል አሰግድ ገልጿል፡፡

በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት የክልሉ ህዝብ ለከፋ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል መዳረጉንም ተናግሯል፡፡

ኮለኔል አሰግድ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱ ይገባል የሚል አቋም እንዳለው ገልጾ ተሳስተውና ተደናግረው ቡድኑን የተቀላቀሉ የፅንፈኛ ቡድኑ አባላትና አመራሮች መንግስት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ተጠቅመው እጃቸውን እንዲሰጡ አሳስቧል፡፡

የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል የሰላምን አማራጭ በመግፋት አሁንም በትጥቅ ትግል በሚገፉ ኃይሎች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቋል፡፡

የሰላም አመራጭን ተቀብለው ለሚመጡ የታጣቂ ቡድን አመራሮች እና አባላት ግብረ ኃይሉ የሚያደርገውን ድጋፍና ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጧል፡፡