የአሜሪካ መንግሥት አዲሱ የአፍሪካ ቀንድ መልዕክተኛ ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው

ጥር 7/2014 (ዋልታ) የአሜሪካ መንግሥት አዲሱ የአፍሪካ ቀንድ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ እና ረዳት ጸሐፊ ሞሊ ፊ ኢትዮጵያና ሱዳንን በሚቀጥለው ሳምንት ሊጎበኙ መሆኑ ተገለፀ፡፡

ጉብኝቱ ለተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ ዓለም ዐቀፍ ድጋፍ ለማድረግ እና በሱዳን በሲቪል መር አስተዳደር ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግን ሽግግር ለማመቻቸት ያለመ ነው ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ሊመክሩ እንደሚችሉ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

ሁለቱ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንደሚጓዙም ተነግሯል፡፡

ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ስለአዲሱ መልዕክተኛ ጉብኝት የተባለ ነገር የለም፡፡

የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ የቀድሞው ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፊልትማን ከሳምንት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውና በጉብኝት ላይ እያሉ ከሥልጣን ተነስተው  በዴቪድ ሳተርፊልድ መተካታቸው ይታወሳል፡፡