የአሜሪካና ፅንፈኛ ምዕራባዊያን ተቋማት ለአሸባሪው ትሕነግ መጮኽን ቀጥለዋል

ታኅሣሥ 16/2014 (ዋልታ) የአሜሪካና ፅንፈኛ ምዕራባዊያን አገራት መገናኛ ብዙኃን ለአሸባሪው ትሕነግ የወገነ ዘገባ ማሰራጨታቸውን ስለመቀጠላቸው እየተመለከትን ነው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተናገሩ።
“የሀሰት መረጃ በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ያሳደረው ጫና” በሚል መሪ ሃሳብ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴርና ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጁት የምክክር ጉባኤ በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ መሆኑን ኢዜአ አስታውሷል።
ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል መንግሥት የአገርና የሕዝብን አንድነት ለማስጠበቅ የሚሰራውን ወደ ጎን በመተው ለአሸባሪ ቡድኑ የወገነ ዘገባ ማሰራጨታቸው የተለመደ መሆኑን እያየን ነው ብለዋል።
አሸባሪ ቡድኑ ግፍና በደል የተፈፀመበትን የአማራና የአፋር ሕዝብ ወደ ጎን በመተው ጩኸታቸው ሁሉ ለወራሪው መሆኑ አሳዛኝ ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል።
የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፍሬው ተገኘ (ዶ/ር) በበኩላቸው አሸባሪው ትሕነግ በየጊዜው የሚነዛው የሃሰት መረጃ በማኅረሰባችን ላይ ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው ብለዋል።
በሚነዛው የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ኅብረተሰቡ ሃብትና ንብረቱን እየተወ በመፈናቀሉ ለተለያዩ ችግሮች መዳረጉን አውስተው ይሄን እኩይ ድርጊት በጋራ መመከት ይገባል ብለዋል።