የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የህዳሴ ግድብን ከደለል ለመጠበቅ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል – ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)

ነሐሴ 17/2016(አዲስ ዋልታ) የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የህዳሴ ግድብን ከደለል ለመጠበቅና ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተለያዩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ተጠሪ ተቋማት ከሱሉልታና አካባቢው ነዋሪ ጋር በመቀናጀት ችግኝ ተከላ አከናውነዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት፣ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴር እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሁም ተጠሪ ተቋማት ናቸው አካባቢውን በእጽዋት ለማልማት ችግኞችን የተከሉት።

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ሸዋ ዞን በሱሉልታ ወረዳ ወሬርሶ ማሊና ቀበሌ ልዩ ሥሙ ሞዬ አካባቢ ነው ችግኞቹ የተተከሉት።

አባገዳዎች ፤ ሽማግሌዎች፤ ወጣቶችና ሕጻናት በችግኝ ተከላው ተሳትፈዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የህዳሴ ግድብን ከደለል ለመጠበቅና ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ገለጸዋል፡፡

ለነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ የሚተላለፍ አሻራ የሚቀመጥበት ታሪካዊ እለት መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ አረንጓዴ አሻራቸውን ያኖሩ ተቋማትንና የአካባቢውን ማህበረሰብ አመስግነዋል፡፡

በዐምደወርቅ ሽባባው