የአርበኞች ተጋድሎና ታሪክ ኢትዮጵያዊያን ያለምንም የሃይማኖትና የብሔር ልዩነት በአንድነት የተዋደቁለት ነው ተባለ

ሚያዝያ 26/2014 (ዋልታ) የአርበኞች ተጋድሎ እና ታሪክ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ያለምንም የሃይማኖት እና የብሔር ልዩነት በአንድነት የተዋደቁለት ነው ተባለ፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት የአርበኞችን ተጋድሎ የሚዘክር የመዛግብት አውደ ርዕይ አዘጋጅቶ ለእይታ አብቅቷል፡፡
በአውደ ርዕዩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ የአርበኞችን ቀን ስናስብ ለሀገር ክብር ብለው ብዙ ኢትዮጵያዊያን አጥነታቸውን ከስክሰዋል፣ ደማቸውን አፍሰዋል፣ ትውልድና መንግሥታት አልፈዋል ለዚህም ለአርበኞች ክብር ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የአርበኞች ተጋድሎ እና ታሪክ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ያለምንም የሃይማኖት እና የብሔር ልዩነት በአንድነት የተዋደቁለት በመሆኑ ይህንን ድንቅ ታሪክ ለአዲሱ ትውልድ በማስተላለፍ ለሀገራችን ዘብ ልንቆም ይገባል ሲሉም አክለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በአባት አርበኞች ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት መሆኑን የጠቀሱት ማኅበሩ ፕሬዝዳንት ሀገር ችግር ውስጥ ስትገባ መታደግ እና ወጣቱን ማስተማር እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሀገር አሁን ላይ የሚገጥማትን ችግር ለመመከት ቀደምት ታሪኮችን በመመልከት እና መጽሓፍትችን ለትውልድ በማስተላለፍ የሀገርን ትክክለኛ ታሪክ ጠንቅቆ ማወቅ እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ይኩኖአምላክ መዝገቡ ናቸው፡፡
በአመለወርቅ መኳንንት