የአስር አመታት መሪ እቅድ ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካለቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ ያለመ ነው- ዶክተር ፍጹም አሰፋ

                                                                                 ዶክተር ፍጹም አሰፋ

እየተከናወነ ያለው የአስር አመታት መሪ እቅድ ድህነትን በግማሽ በመቀነስ ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካለቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ ያለመ ነው ሲሉ የብሔራዊ ፕላንና ልማት እቅድ ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለጹ።

የአስር አመታት የልማት መሪ እቅድ አካታችና ጥራት ያለው ምጣኔ ሃብት እድገት፣ ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ተቋማት እድገት፣ የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታና የዲጂታል ኢኮኖሚ እድገት ምሰሶዎችን ያካተተ መሆኑንም ኮሚሽነሯ ተናግረዋል፡፡

የብሔራዊ ልማትና እቅድ ኮሚሽነሯ ዶክተር ፍጹም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በፖሊሲ ማተር ቆይታ ያደረጉ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች እድገት ብታስመዘግብም የተመዘገቡት ለውጦች ግን እያንዳንዱ ዜጋን ተደራሽ ያደረጉ ባለመሆናቸው በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ የዴሞክራሲና የተጠቃሚነት ጥያቄዎች ማስነሳቱን ገልጸዋል።

በዚህም እያደገ ያለው ኢኮኖሚ ሁሉን አካታች እንዲሆንና የተጠቃሚነት ጥያቄዎችን ለመመለስ የለውጥ ስራ መስራት አስፈልጓል ነው ያሉት።

ፖሊሲው የስራ አጥ ቁጥርን 9 በመቶ ለማድረስ እንደሚሰራና በመሰረተ ልማት  ዘርፍም ሰፊ ተግባራት እንደሚከናወኑ አስታውቀው፤ ለአብነትም በሃይል ልማት ዘርፍ በከተማና በገጠር 20 ጊጋ ዋት ሃይል ለማመንጨት መታቀዱን ጠቁመዋል።

በማህበራዊ ዘርፉ ደግሞ በጤና፣ በትምህርትና በአቅም ግንባታ ተግባራት ላይ ፖሊሲው እንደሚያተኩርና ሌሎችንም ግቦች ያካተተ ነው ብለዋል።

ይህንን ለማሳካት መሪ እቅዱ ሰፊ ምሰሶዎችን መያዙን ጠቁመው አካታች እና ቁልፍ ጥራት ያለው የምጣኔ ሃብት እድገት፣ የተናጠል ግብና ምርታማነት፣ ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ተቋማት እድገት፣ የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታና ዲጂታል ኢኮኖሚ እድገት መካተቱን አስረድተዋል።

የግል ሴክቴሩን ከፊት ቀዳሚ ማድረግ፣ አረንጓዴ ልማት፣ ተቋማዊ ግንባታ እንዲሁም የፍትህና ህዝባዊ አገልግሎት ማግኘት፣ ማህበራዊ አካታችነትና ማብቃት፣ በቀጠናው አካባቢ ልማትና ትስስር መፍጠር እንዲሁም  የጸጥታና ደህንነት ግንባታ ምሶሶዎችን መሪ እቅዱ ማካተቱን ነው የገለጹት።

የመንግሰት እቅድ ብቻ ሳይሆን ህዝቡንና ባለ ድርሻ አካላትን እንዳካተተ የገለጹት ዶክተር ፍጹም፣ ቀድሞ ተሰርቶ የሚሰጥ ሳይሆን ተቋማትና በላድርሻ አከላት ራሳቸው የሚያዘጋጁት ነው ብለዋል።

መሪ እቅዱ ከ100 በላይ ከፍተኛ አማካሪዎች ጋር በመሆን መዘጋጀቱን ገልጸው፣ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ውጤትን መሰረት ያደረገ ምዘናን በስሩ ያካተተ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡