የአሸባሪ ቡድኑ ዓላማ ኢትዮጵያን ማፍረስ፣ ሕዝቡን ማዋረድና ትግራይን በተዘረፈ ሃብትና ንብረት መገንባት ነው – አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

ነሃሴ 18/2013(ዋልታ) – አሸባሪው የትህነግ ቡድን በአማራ ክልል ወረራ ከፈጸመበት ጊዜ አንስቶ በሰሜን ወሎ፣ በዋግኽምራ፣ በሰሜን ጎንደር እና በደቡብ ጎንደር ዞኖች ከፍተኛ ውድመት አድርሷል፡፡

በሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ማኅበራዊ ጥቃት ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡

“ኢትዮጵያ ውስጥ በተካሄደ የውጪ ወረራ በዚህ መልኩ ኅብረተሰብን ለማደህየት፣ አካባቢን ለማራቆት ሆን ተብሎ የተሠራ ሥራ ተጽፎ አላነበብኩም፤ አይቼም አላውቅም”ብለዋል፡፡

የወራሪው እና አሸባሪው ትህነግ አባላት የመንግሥት ተቋማትን አፍርሰዋል፤ የሕዝብ መገልገያ ተቋማት የጤና፣ የትምህርት፣ የግብርና እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ሙሉ በሙሉ እንደዘረፉትም አንስተዋል፡፡

ቆቦ፣ ወልድያ፣ ኮን፣ መቄት፣ ላልይበላ፣ ሰቆጣ፣ ነፋስ መውጫ፣ አዲ አርቃይ እና መርሳ የሚገኙ ሆስፒታሎች ከጣሪያና ግድግዳቸው ውጪ ሁሉንም ቁሳቁስ ዘርፈው ወደ ትግራይ ጭነዋል፡፡

የትምሕርት ቤት ቁሳቁስ፣ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማትም ሙሉ በሙሉ ተዘርፈዋል፡፡

የኤሌክትሪክና የስልክ መሠረተ ልማቶችን ጨምሮ የልማት አውታሮች ተሰርቀዋል፣ ማጓጓዝ የማይችሉትንም ከጥቅም ውጪ አድርገዋል ብለዋል አቶ ገዱ፡፡

አቶ ገዱ እንደገለጹት የሽብር ቡድኑ አባላት “የግለሰብ ካልሲን” ጨምሮ ለርዳታ የቀረበን ሃብት ሳይቀር ዘርፈዋል፤ የሕዝብ ተቋማት ሳይቀሩ ተሰርቀዋል ፣ይህንን እያደረጉ አርሶ አደሩን “ከእናንተ ጋር ጸብ የለንም” እያሉ  ለማታለል ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡

አቶ ገዱ እንዳሉት ከጋይንት እስከ ቆቦ ታጥቀው ትግል ያላደረጉና የፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸው በርካታ ንጹኃን ሰዎች ተገድለዋል፤ ሴቶችም ተደፍረዋል፡፡

ኅብረተሰቡ በየቀኑ የሚደርስበት ማሸማቀቅ በአንድ ሀገር አብሮ የኖረ ቀርቶ ከሌላ ሀገር ለመውረር የሚገባ እንኳ ሊያደርገው የማይችል አጸያፊ ድርጊት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ሽብርተኛው ትህነግ ሕዝቡ አንገቱን እንዲደፋ፣ ለዘመናት እንዳያንሰራራ በኢኮኖሚ የማዳከም እና ሞራሉን የማላሸቅ ዓላማ ይዞ እየሠራ መሆኑን በማሳያነት ተናግረዋል፡፡

የአሸባሪ ቡድኑ ዓላማ ኢትዮጵያን ማፍረስ፣ ሕዝቡን ማዋረድ፣ ትግራይን በተዘረፈ ሃብትና ንብረት መገንባት መሆኑን በመጥቀስም ሁሉን አቀፍ ውድመትና ጥፋት በኅብረተሰቡ እየፈጸመ ስለመሆኑም ተጨባጭ መረጃ እንዳለ አቶ ገዱ አመላክተዋል፡፡ ሕዝቡም ይህንን መገንዘቡን ጠቅሰዋል፡፡

አሸባሪው ትህነግ ወረራ የፈጸመው በትጥቅ ትግል ፖለቲካዊ ስልጣን ለመያዝ ወይንም ከገዢው ፓርቲ ጋር ባለው ጥላቻ ብቻ የሚመስለው ካለ ስህተት እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ገዱ ሁሉም የችግሩን መጠን በልኩ ማወቅ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

አቶ ገዱ እንደገለጹት ሽብርተኛው ትህነግን ለመደምሰስ በዚህ ጊዜ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ፍልሚያ እያካሄደ ነው፤ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻና ፋኖ እንዲሁም ከየክልሎች የተውጣጡ የልዩ ኀይል አባላት በቅንጅት እየሠሩ ነው፡፡ ያለ የሌለ ኀይሉን አሟጦ እየተፍጨረጨረ ያለውን ግብስብስ እና ወራሪውን ትህነግ በማጥፋት ሀገር ወደ ተረጋጋ ሁኔታ እንድትመለስ እየተደረገ ያለው ፍልሚያ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡