የአሸባሪው ህወሓት ዘረፋ በምርት ገበያ መጋዘኖች

ኢንጂነር ኢሌሮ ኡፒየው

መስከረም 7/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ህወሓት የምርት ገበያ ቢሮዎችን ከጥቅም ውጭ ከማድረጉም በላይ በመጋዘኖች ውስጥ የተከማቹ ምርቶች መዝረፉን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን አስታወቀ።

ባለሥልጣኑ በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ባሉት 27 ጥብቅ መጋዘኖች ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች አከማችቶ ለሽያጭ የሚያቀርብ ሲሆን፣ የተዘረፈው የግብርና ምርቶች ከ24 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ እንደሚገመት ተጠቁሟል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ኢሌሮ ኡፒየው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አሸባሪው ህወሓት በሁለት ማከማቻ መጋዘኖች የነበረ ከ24 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ምርት በመዝረፍ የተቋሙን ቢሮዎች አውድሟል።

ቡድኑ ከሽራሮ እና ሑመራ የምርት መረከቢያ መጋዘኖች ከ4 ሺሕ 822 ኩንታል በላይ ምርት መዘረፉን ነው የገለጹት።

አርሶ አደሩ ምርቱን በመሰብሰብ ላይ እንዳለ አሸባሪው ቡድን “በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈፀሙ ለውንብድና ተግባሩ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮለታል” ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

ይህ ተግባሩ በአገር ኢኮኖሚና በምርት ገበያው ስራ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከመፍጠሩ ባሻገር አርሶ አደሩንም ለኪሳራ መዳረጉን ተናግረዋል።

በምርት ገበያው መጋዘኖች ላይ የተፈፀመው ዘረፋ የምርቱን ባለቤቶች በተለይም አርሶ አደሩን ለመጉዳትና ተጠቃሚ እንዳይሆን ለማድረግ መሆኑን ሕብረተሰቡ መገንዘቡንም አንስተዋል።

አሸባሪው ቡድን የዘረፈውን እህል የቻለውን በመውሰድ ያልቻለውን በየቦታው በመበተን ከጥቅም ውጭ ማድረጉንም ጠቁመዋል።

የጥፋት ቡድኑ ከዘረፋው በተጨማሪ ምርት ገበያው አርሶ አደሩ ለገበያ የሚያቀርበውን እህል ሰብስቦ የሚያስቀምጥባቸውን መጋዘኖችም ማውደሙን ኢንጂነር ኡሌሮ ተናግረዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ በምርታቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው አካላት ለመንግስት የካሳ ጥያቄ እያቀረቡ  ነው።

ባለስልጣኑ ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አሳውቆ ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን አመራርና ሠራተኞች ለመከላከያ ሠራዊቱ የአንድ ወር ደመወዝና የደም ልገሳ ያደረጉ ሲሆን፣ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።