የአሸባሪው ሕወሓትን የጥፋት ጉዞ ለማስቆም እንደሚዘምቱ የባሕር ዳር ከተማ መንግሥት ሠራተኞች ገለጹ

የባሕር ዳር ከተማ መንግሥት ሠራተኞች

ጥቅምት 24/2014 (ዋልታ) የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ከከተማ አስተዳደሩ የመንግሥት ሠራተኞች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

ውይይቱን የመሩት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳኅሉ (ዶ/ር) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል እያደረሰ ያለውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ጥፋት ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን በሥልጣን ዘመኑም ሲያደርገው የነበረ እና ሥር የሠደደ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል አማራን በጠላትነት ፈርጆ ሀገር የማፍረስ እኩይ ተግባሩን እየፈጸመ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

አሸባሪው የሕወሓት ኃይል ታሪካዊ ጠላት በመሆኑ ይህን ታሪካዊ ጠላት ለመቅበር የመንግሥት ሠራተኛው በግንባር በመሠለፍ፣ ሃብት በማሰባሰብ እና ድጋፍ በማቅረብ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዚህም ቃላችንን ወደ ተግባር በመቀየር የአማራን አይደፈሬነት እና አይበገሬነት ልናሳይ ይገባል ብለዋል፡፡ የህልውና ዘመቻው የመጨረሻው ግብ አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ኃይል ከአማራ ክልል ማስወጣት ብቻ ሳይሆን ለአማራ ብሎም ለሀገር ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ማድረስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ጌትነት ባምላኩ የአሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ኃይል የከፈተውን ወረራ ለመቀልበስ የሁሉንም ተሳትፎ ስለሚጠይቅ እርሳቸውም ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የአሸባሪውን ኃይል ሰርጎ ገቦች ለማጋለጥ እና ለማደን ሕዝብ እና መንግሥት በቅንጅት መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ደመቁ ተቀባ የሚሠጣቸውን ተልዕኮ ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ኃይል በአጭር ጊዜ ለመደምሰስ ሁሉም አካባቢውን ነቅቶ ከመጠበቅ ጀምሮ ለሕልውና ዘመቻው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡