የአሸባሪው ሸኔ ታጣቂ የነበሩ አባላት በይቅርታ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቀሉ

ኅዳር 17/2014 (ዋልታ) በምዕራብ አርሲ ዞን ሄባን አርሲ ወረዳ የአሸባሪውን ሸኔ እኩይ ዓላማ የተረዱ የቡድኑ አባላት በይቅርታ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቀሉ።

የአሸባሪው ዓላማ የማይጠቅም በመሆኑ ወጣቶች ከቡድኑ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በመተው ሕብረተሰቡን በይቅርታ እንዲቀላቀሉ የአካባቢው አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሀደ ስንቄዎች ያቀረቡት ጥሪ ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል።

አሁን በይቅርታ ሕብረተሰቡን የተቀላቀሉ ወጣቶች ከአሸባሪው ሕወሓት የሽብር ተልዕኮ ወስደው ሕብረተሰቡ ላይ ጉዳት በማድረሳቸው መጸጸታቸውን ገልጸዋል።

ሌሎች ከቡድኑ ጋር የተሰለፉ ወጣቶችም ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ መክረዋል።

የሄባን አርሲ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አወል ዋፎ እንዳሉት ወጣቶቹ በፈጸሙት የሽብር ድርጊት ተፀፅተውና የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ዛሬ ከማሕበረሰቡ ጋር በይቅርታ መቀላቀላቸው ትክክለኛ ውሳኔ ነው።

የምዕራብ አርሲ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አህመድ ሃጂ በበኩላቸው በአሁኑ ሰዓት በርካታ ወጣቶች የአሽባሪዎች እኩይ ዓላማ በመረዳት እጃቸውን በሰላማዊ መንገድ መስጠት መጀመራቸው ተናግረው፤ ከቡድኑ ጋር ተቀላቅለው የሚገኙ ወጣቶች የጓደኞቻቸውን ፈለግ ተከትለው ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡