የአሸባሪውን ሕወሓት ግብዓተ መሬት ለመፈጸም በጋራ መነሳት አገራዊ ግዴታ ነው!

ጥቅምት 22/2014 (ዋልታ) የአሸባሪውን የሕወሓት ቡድን ግብዓተ መሬት ለመፈጸም በጋራ መነሳት አገራዊ ግዴታ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ።
ፓርቲው ያወጣው መግለጫ ቀጥሎ ቀርቧል፦
አሻባሪው የትህነግ ቡድን ባለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያን በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጎሳና በጎጥ ከፋፍሎ ሲመዘብር መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ቡድን እኔ ያልመራኋት ኢትዮጵያ ትጥፋ በሚል እሳቤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያለ የሌለውን ኃይል አሰባስቦ ዘምቶብናል።

ባለፉት 3 የለውጥ ዓመታት በከፍተኛ መስዋእትነት የተገኘውን ሀገራዊ ለውጥ ለመቀልበስ በተለያዩ ጊዜያት ሞክሮ ያልተሳካለት ይሄው አሸባሪ ቡድን ጥቅምት 24/2013 ዓ ም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የሚገኘውን የሰሜን እዝ የሃገር መከላከያ ሰረዊታችን ላይ ጥቃት በመሰንዘር ኢትዮጵያውያን በይፋ መውጋት ከጀመረ ድፍን አንድ ዓመት ሊሞላው ዋዜማው ላይ እንገኛለን።

በሰሜን ዕዝ ጥቃት እጅግ የተቆጣው የሃገር መከላከያ እና መላው ህዝባዊ የፀጥታ ሃይሎቻችን በተወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ የጥቃቱ ጠንሳሾችና ባለቤቶችን ለሕግ ማቅረብ፣ እርምጃ በመውሰድና የቀሩትን መበተን ቢቻልም፣ በሕግ ማስከበሩ የተጎዱ የትግራይ አከባቢዎችን መልሶ ለማቋቋምና አርሶ አደሮች እርሻቸውን ተረጋግተው እንዲያርሱ የተወሰደውን የአንድ ወገን ተኩስ አቁም አሸባሪ ቡድኑ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በመላው የአፋር እና የአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ወረራውን አስፋፍቷል፡፡

በዚሁ መሰረት ጁንታው የትህነግ ቡድን በፈጸማቸው አረመኔያዊ ጥቃቶች ንጹሐን ተገድለዋል፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፣ በሰው ልጅ ላይ ለመፈፀም ቀርቶ ለማሰብ የሚከብዱ አስነዋሪ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን በመፈፀም እኩይ ተግባሩን በግልጽ ከማሳየቱም አልፎ ለዘመናት የተገነቡ የህዝብ መሰረተ ልማቶችን በመዝረፍና የተቀረውን በማውደም ኢትዮጵያን ለማዋረድና ሀገራችንን ለማፍረስ እኩይ ተግባሩን በስፋት ቀጥሎበታል። በሴቶች እህቶቻችን ላይ አሳዛኝና አስነዋሪ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ተፈጽሟል።

ይህ ቡድን ከተቻለ ኢትዮጵያዊያንን በኃይል በማንበርከክ ወደ ቀድሞ ስልጣን ለመመለስ ካልሆነ እሱ ያልመራትን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የኢትዮጵያን አንድነትና ጥንካሬ የማይፈልጉ ታሪካዊ የውጪ ጠላቶችና የውስጥ ባንዳዎችን አስተባብሮ የክህደት ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥቷል።

ስለሆነም በሀገር ሉዓላዊነት ላይ ድርድር የማያውቀውን ሕዝባችን በዘር፣ በፖለቲካና በሃይማኖት ሳይለያይ አሸባሪው የህወሓት ጁንታ ቡድን ሀገር ለማፍረስ በያዘው እቅድ በአሁኑ ወቅት በአማራና አፋር ክልል ሕዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ጥፋት በጋራ በመመከት ጁንታውን ግብዓተ መሬቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፈጸም በጋራ መነሳት ሃገራዊ ግዴታችን ነው።

የክልላችን ብልጽግና ፓርቲ አመራሩ፣ አባሉና መላው የክልላችን ነዋሪዎች በማስተባበር ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በሰው ኃይል፣ በአይነት፣ በገንዘብና በሞራል እየደገፈ የቆየ ቢሆንም ካለው ወቅታዊ አሳሳቢ የህልውና ጉዳይ ይህንን የህዝባችን ጠላት የሆነውን የጥፋት ቡድን ግብዓተ- መሬቱን ለማፋጠን የጀመርነውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል።

በመሆኑም ወገናችን የሆንከው የትግራይ ህዝብ ከሠላም ወዳዱ ህዝባችን ጎን በመቆም በልጆችህ ህይወት ቁማር የሚጫወት እና ለአንድነታችን፣ ለሠላም፣ ሉዓላዊነት ነቀርሳ የሆነውን ይህን የጥፋት ቡድን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ እየተደረገ ባለው ርብርብ ከጎናችን እንድትሆኑ ወንድማዊ ጥሪ እያቀረብን በሌላ በኩል የልማታችን ፀር የሆነውን የጁንታውን ቡድን በአጭር ጊዜ ውስጥ ደምስሰን ፊታችንን ወደ የልማት ተግባሮቻችን ለመመለስ የክልላችን ሕዝቦች ከሀገር መከላከያ ጎን እንዲቆም የክልሉ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ጥሪውን ያስተላልፋል።

የክልላችን ፀጥታ አካላትና ወጣቶች ክልላችን ጋምቤላ ድንበር ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በውስጥ የጋምቤላ ነፃነት ግንባር፣ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችና የጁንታውን ዓላማ የሚያራግቡ ጥቂት ፀረ-ሠላም ኃይሎች የሚንሳቀሱበት በመሆኑ በውጪ የዘመናት ታሪካዊ ጠላቶቻችን በቅርበት የሚገኙበት በመሆኑ በንቃት አካባቢያችንን እንድትጠብቁ እና የጀመርነውን ሁሉን አቀፍ የልማት እንቅስቃሴ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጋራ ሰላም ለማስከበር ለሚደረገው ጥረት የኅብረተሰቡን ፀጥታና ደህንነት በመጠበቅ ሃገራዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ያሳስባል።

የጋምቤላ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት
ጥቅምት 22/2014 ዓ.ም
ጋምቤላ
_ ጠብቅ፣ ዝመት ደግፍ
_ አካባቢህን ጠብቅ
_ ወደ ግንባር ዝመት
_ መከላከያን ደግፍ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት፦