የአሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ የጥፋት ጥምረትን በጽናት መታገል ይገባል ተባለ

ነሐሴ 11/2013 (ዋልታ)- አሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ የፈጠሩትን የጥፋት ጥምረት መታገል እንደሚገባ በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ ገለጹ፡፡
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ምክክር እያደረጉ ነው፡፡
በመድረኩ ላይ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከሸኔ ጋር ጥምረት በመፍጠር እየፈፀመ ያለውን የሽብር ተግባር በጽናት መታገል እንሚገባ አሳስበዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ በጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸም ጦርነት እንዲፈጠር ማድረጉን አስታውሰው ከሸኔ ጋር ጥምረት በመፍጠር የሽብር ተግባሩን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኩሴ ጉዲሼ ህወሓት መራሹ ቡድን በሚያራምደው የሴራ ፖለቲካ መላው ህዝብ ለችግር ተጋልጧል ብለዋል፡፡
ቡድኑ ሀገሪቱን ለመበታተን በማለም የሽብር ተግባር ሲሰራ እንደነበርም ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ የምሁራን ዲፕሎማሲ የሀገርን ህልውና ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረት ወደ አንድ ምዕራፍ ለማሳደግ ሚናው የጎላ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን የሽብር ቡድኑ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል ሲል የዘገበው የደቡብ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው፡፡