የአሸባሪዎች ፍላጎት እና ጥፋት የአማራ እና ኦሮሞ ሕዝቦች አንድነትን እንደማይሸረሽር ተገለጸ


ሰኔ 20/2014 (ዋልታ)
የአሸባሪዎች ፍላጎት እና ጥፋት የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝቦች አንድነትን እንደማይሸረሽር ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ የተጨፈጨፉት ንጹሃን ወገኖች በመጀመሪያ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ ቀጥሎ ኢትዮጵያዊ ናቸው፤ ይህን ደግሞ በጋራ አውግዘናል ብለዋል።

ሸኔ የአማራ ብቻ ጠላት ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጠላት እንደሆነ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ሸኔን ከማጥፋት ውጭ አማራጭ እንደሌለ ተወያይተናል፤ አቅጣጫም አስቀምጠናል ብለዋል።

አሸባሪው ሕወሓት ጦርነት እየጎሰመ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንንም መመከት የምንችለው በጋራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው ከዚህ በፊት የሁለቱ ሕዝቦች አብሮነት እየተገመደ እንጅ እየላላ አልሄደም፤ አሸባሪው ሕወሓት ሲነሳ አንድነታችን ጠንክሮ በአንድ ጉድጓድ እንደተቀበርን አሸባሪው ሸኔ ሲነሳም አንድነታችን የበለጠ እንዲጠናከር አድርጎታል ብለዋል።

ሸኔ ጊምቢ ላይ ጥቃት የፈፀመው ሦስት ዓላማዎችን ይዞ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ አንደኛ የአማራና የኦሮሞ ሕዝብን ለመለያየት ሲሆን ይህ ትላንት ሕወሓትም አስቦ ያልተሳካለት ሸኔም ዛሬ የማይሳካለት በእኛ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የማይሆን ነው ብለዋል።

ሁለተኛው ፍርሃትን በሀገሪቱ ማንገስ ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ ማሸበር ነው ብለዋል። ይህ እንዳይሳካ በጋራ ርምጃ እየወሰድን ነው ያሉት፡፡

ዛሬ አንድነታችንን የምናሳየው ጽንፈኝነትን በመዋጋት ነው ብለዋል። ለሕዝባችን ለዓላማችን ስንል ትላንት መስዋእትነት እንደከፈልነው ነገም መስዋእትነት ከፍለን ኢትዮጵያን የተሻለች ሀገር እናደርጋለን ነው ያሉት።

ሸኔን ሽፋንና መረማመጃ አድርገው በአመራሩ ላይ የሚዘምቱ አመራሩን ለመከፋፈል የሚጥሩ አይሳካላቸውም ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡