የአቡነ መርቆሪዎስ ሥርዓተ ቀብር መጋቢት 4 በቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን እንደሚፈጸም ተገለጸ

የካቲት 29/2014 (ዋልታ) የአቡነ መርቆሪዎስ ስርዓተ ቀብር መጋቢት 4 በቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን እንደሚፈጸም ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ 4ኛው ሊቀ ጳጳስ አቡነ መርቆሪዎስ የካቲት 25 ከዚህ ዓለም በድካም ማረፋቸው ከተሰማ በኃላ የቀብር አፈፃፀሙን በተመለከተ ኮሚቴ ተዋቅሯል።
በዚህም 12 ዓብይ ኮሚቴና አምስት ንዑስ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
የአቡነ መርቆሬዎስ አስከሬን ሽኝት ቅዳሜ መጋቢት 3 በመስቀል አደባባይ እንደሚደረግ የገለጹት ዋና ፀሐፊው የሽኝት መርሃ ግብሩ ከ3 ሰዓት እስከ 7 ሰዓት ከ45 ደቂቃ እንደሚቆይ ተናግረዋል።
በዚህ መርሀ ግብር የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የእህት ዓብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉም ተብሏል።
ከመስቀል አደባባይ የአስከሬን ሽኝት በኋላ በመንበረ ፓትሪያርክ ፀሎተ ወንጌል እንደሚደረግ የገለጹ ሲሆን ምሽት ደግሞ በቅድስት ስላሴ ካቴደራል ቤቴክርስቲያን ፀሎትና ፍትሀት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
በመጨረሻም እሁድ መጋቢት 4 የተለያዩ ዝግጅቶች ከተከናወኑ በኋላ ሥርዓተ ቀብር እንደሚፈፀም ተገልጿል።
በምንይሉህ ደስይበለው