የአካባቢ ጥበቃ ሥራን በተደራጀና ቀጣይነት ባለው መንገድ መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ

የካቲት 7/2014 (ዋልታ) “የወጣቶች ንቁ ተሳትፎና ባለቤትነት ለዘላቂ የአካባቢ ጥበቃና ልማት” በሚል መሪ ቃል በባቱ ከተማ ከመላው የኢትዮጵያ አካባቢ ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር በአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ምክክር እየተደረገ ነው።

በየጊዜው እየተፈራረቀ የመጣውን የድርቅና የጎርፍ አደጋ መብዛትን ለመከላከል የአካባቢ ጥበቃን በተደራጀ መንገድ መሥራት እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

የአካባቢ ጥበቃ ሥራን ውጤታማ ለማድረግ ደግሞ ወጣቶች በየአካባቢያቸው ንቃተ ህሊናን በማሳደግ ንቅናቀን በመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረግ እንዳለባቸውም ተጠቁሟል።

በህገ መንግስቱ አንቀፅ 44 ዜጎች በንፁህና ጤናማ አካባቢ መኖር አለበት የሚለውን ወደ ተግባር በመቀየር እና ለሀገር እድገት የሚሰሩ ልማቶችም ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃን ባማከለ መንገድ እንዲሰሩ ማድረግ ይገባልም ተብሏል።

በኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ላይ እንቅፋት እየፈጠሩ ካሉ ጉዳዮች መጤ ወራሪ አረም አንድ መሆኑ በምክክር መድረኩ ተነስቷል።

በተለያዩ ጊዜያት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ 35 መጤ ወረሪ አረሞች ሲኖሩ ሰባት የሚሆኑት ከፍተኛ የሆነ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸውም በመድረኩ ተገልጿል። መጤ አረሞች 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ወረው እንደሚገኙም ነው የተነገረው።

በተለይ በአፋር አካባቢ በብዛት የሚታየው የወያኔ ዛፍ ተብሎ የሚጠራው አረም በአፋር አካባቢ ከታየበት ጀምሮ 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ብር ማሳጣቱ ተገልጿል።

የእንቦጭ አረምም ቢሆን በጣና፣ በዝዋይና መሰል ሀይቆች ላይ ከፍተኛ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳት እያደረሰ ነው ተብሏል።

ምክክሩን የኢትዮጵያ ወጣቶች ሊግ ከኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ማዘጋጀቱ ተመላክቷል።

ምንይሉ ደስይበለው (ከባቱ)