የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ለ”ህልውና ዘመቻ” ከ17 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

ሐምሌ 16/2013 (ዋልታ) – የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ለ”ህልውና ዘመቻ” ባዘጋጀው የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ከ17 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡ ገለጸ።
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮችን በማካሄድ 278 ሚሊየን ብር በጥሬ እና በዓይነት በማሰባሰብ ድጋፍ ለማድረግ አቅዶ ወደ ሥራ ገብቷል።
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የድጋፍ አሰባሰብ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እንግዳ ዳኛው ህዝብን ከአሸባሪው ህወሓት ለመጠበቅ የሚከናወኑ ተግባራት በህብረተሰቡ ሙሉ ተሳትፎ መደገፍ አለበት ብለዋል።
እስካሁንም አርሶ አደሩንና የንግዱን ማህበረሰብ ብቻ በማነቃነቅ 17 ሚሊየን 407 ሺህ ብር ድጋፍ መሰብሰቡን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በዞኑ ከሚገኙ የመንግስት ሠራተኞች ውስጥ 99 በመቶ የሚሆኑት የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመለገስ በመወሰናቸው 118 ሚሊየን 562 ሺህ ብር እንደሚሰበሰብ ማስረዳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።