የአዋሽ ወልዲያ ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት በባቡር ቴክኖሎጂና በሲቪል ስራዎች የእውቀት ሽግግር የተደረገበት መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
በሚኒስቴሩ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ቡድን የባቡር ፕሮጀክቱ በሚተገበርበት ወቅት የተካሄዱ የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን ጎብኝተዋል።
ቡድኑ በተለይም በባቡር ቴክኖሎጂና በሲቪል ስራዎች የኢትዮጵያ ባለሙያዎች እውቀትን ከማሸጋገር አንፃር እና ስራውንም በመምራትና በመፈፀም የነበራቸውን ተሳትፎ በተመለከተ የተሰሩና አርአያ የሚሆኑ ስራዎችን ተመልክቷል::
የባቡር ስራው በትራንስፖርት ዘርፍ ለአገሪቱ ከሚያደርገው አስተዋፅኦ በተጨማሪ ለሌሎች ቴክኖሎጂዎች ልማትም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተጠቁሟል::
ባቡሩን ተከትሎ የተዘረጋው ከ400 ኪ.ሜ በላይ የፋይበር ገመድ ለባቡሩ ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ የዲጂታል አገልግሎቶችን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል ተብሏል።
ከባቡሩ ጋር የተካተቱ ቴክኖሎጂዎች እና የአገልግሎት መስጫ ፋሲሊቲዎች ከሌሎች ተቋማት ጋር በተለይም ከዩኒቨርሲቲ፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በአምራች ዘርፍ ከተሰማሩ ድርጅቶች ጋር በቴክኖሎጂው ዘርፍ በትስስር ለመስራት አመቺ ሁኔታዎችን እንደምፈጥርም ተገልጿል::
ሚኒስቴሩ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲውን እየከለሰ የሚገኝ ሲሆን፣ ፖሊሲው በቴክኖሎጂ ሽግግርና በተቋማት መካከል የሚደረጉ ትስስሮችን የሚያበረታታ መሆኑን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡