የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች አለመምጣት በምርጫው ላይ የሚያጎድለው ነገር የለም- ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ

ሚያዝያ 29/2013 (ዋልታ) – የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች መምጣት አለመምጣት በአገራዊው የምርጫ ሂደት ላይ የሚያሳድረው አንዳችም ተጽእኖ እንደሌለ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ገለጹ።

የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች መምጣት አለመምጣት በአገራዊው የምርጫ ሂደት ላይ የሚያሳድረው አንዳችም ተጽእኖ የለም ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፣ ታዛቢዎች ባሉበት ባለፉት ምርጫዎች ወቅትም ውዝግብን ከመጫር ባሻገር የፈየዱልን አንዳችም ነገር የለም ብለዋል።

በተለይም በ1997ቱ ምርጫ ወቅት የአውሮፓ ህብረት ታዘብኩ ብሎ ያወጣው መረጃ እንደ አገር ብዙ ዋጋ የከፈልንበት ብዙ ትርምስ የተፈጠረበት ከመሆኑ አንጻር አሁን ላይ አንመጣም ማለታቸው የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም ሲሉ አክለዋል።

ብዙ ምርጫን ከመሳተፌ አንጻርና ባለኝ ልምድ ከአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ህብረት ምርጫ ታዛቢ እየተባሉ ቢመጡም የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ሲወጡ አይቼ አላውቅም ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፣ እንደውም አንዳንድ ጊዜ ስራቸውን ሙሉ በሙሉ ዘንግተው እንደ አገር ጎብኚ ቱሪስት ሁሉ ሲያደርጋቸው እንደታዘቡም አመልክተዋል።

ከዚህ የተነሳም እነሱ እየታዘብን ነው በሚሏቸው አካባቢዎች ላይ እንኳን ችግር አለ ተመልከቱልን ሲባሉ ፍቃደኛ የማይሆኑበት ጊዜ ብዙ መሆኑን ገልጸው፣ እንደ እኔ እነዚህ ታዛቢዎች መቅረታቸው እንደውም የውስጥ አቅማችንን ተጠቅመን ምርጫውን ተዓማኒ እንድናደርገው እድል የሚሰጥ ይመስለኛል ማለታቸውን የኢፕድ ዘገባ ያመለክታል።