የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያዊን ዘንድ እንደማይታመን አኔት ሁበር ገለጹ

መስከረም 19/2015 (ዋልታ) የአውሮፓ ሕብረት በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ካራመደው አቋም ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ እንደማይታመን የሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አኔት ሁበር ገልጸዋል፡፡

ልዩ መልዕክተኛዋ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሀመርን ጨምሮ ከሌሎች አለም አቀፍ አጋሮች ከተውጣጡ አካላት ጋር በኢትዮጵያ ያደረጉትን ቆይታ አስመልክተው አራት ገጽ ሪፖርት ለሕብረቱ አባል ሀገራት አቅርበዋል፡፡

ከመስከረም 4 እስከ 6 2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ተስፋዬ ይልማ፣ ከቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ እንዲሁም ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በተጨማም በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ስራ ላይ ከተሰማሩ ዓለም አቀፍ ድርጅት ኃላፊዎች እንዲሁም ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ጋር የመከሩ ሲሆን ከትግራይ ክልል ባስልጣናት ጋር ተከታታይነት ያለው የስልክ ውይይት ማድረጋውን በሪፖርታቸው አካተዋል፡፡

በሪፖርታቸውም የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ በሚንቀሳቀሱ እና ተጽእኖ ፈጣሪ በሆኑ የመንግስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ለአንድ ወገን ያደላ ነው በሚል ተቀባይት እንደሌለው አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም ሕብረቱ ይህን በኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ የተቀረጸውን የሕብረቱ ምስል ለመቀየር በትኩረት መስራት እንደሚገባውም አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡

በነስረዲን ኑሩ