የአውሮፓ ቢዝነስ ፎረም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ፈረመ

መጋቢት 29/2014 (ዋልታ) የአውሮፓ ቢዝነስ ፎረም በኢትዮጵያ በቀጣይ ከመንግሥት ጋር ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ፡፡

የአውሮፓ ቢዝነስ ፎረም በኢትዮጵያ ሊቀመንበር ቤን ዲፓራትሬ እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሬታ ሰዋሰው ስምምነቱን ተፈራርመዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሬታ ሰዋሰው የኢትዮጵያ መንግሥት ከአውሮፓ ቢዝነስ ፎርም ጋር የረጅም ጊዜ አጋርነቱን ለማጠናከር ፍላጉት እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡

በተለይም ትብብሩ የግል ዘርፍ ኢንቨስትመንትን በማጎልበት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

የመግባቢያ ስምምነቱ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል የልምድ ልውውጥ እና የጋራ ምክክር እንዲኖር እንደሚያስችል ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የአውሮፓ ቢዝነስ ፎረም በኢትዮጵያ መሰረታቸውን አውሮፓ ባደረጉ ባለሀብቶች ተቋቁሞ ሥራውን እ.አ.አ በ2012 የጀመረ ሲሆን ዋና አላማውም ኢትዮጵያን ለአውሮፓ ባለሀብቶች ተመራጭ መዳራሻ ማድረግ ነው፡፡