የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመከላከል የሴቶች ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበት ተገለጸ

መጋቢት 7/2014 (ዋልታ) የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመከላከል የሴቶች ተሳትፎና የአመራር ሰጪነት ሚና መጠናከር እንዳለበት የኢፌዴሪ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሯ በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው የአየር ንብረት ለውጥ በሴቶች ላይ የሚያደርሰውን ተጽእኖ በመከላከልና ሴቶች በሚኖራቸው ሚና ላይ ባተኮረ ስብሰባ ላይ የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የሴቶችን እምቅ አቅምና እውቀት በማቀናጀት በአየር ንብርት ለውጥ ምክንያት የሚደረሰውን ከባቢያዊ ጉዳት ማስቀረት ያስችላል ብለዋል።
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያየዘ በሴቶችና በአከባቢያቸው ላይ ተግዳሮትን ሊፈጥሩ የሚችሉ ጉዳዮችን ቅድሚያ ሰጥቶ መመለከት እንደሚገባና ከማኅበራዊ አገልግሎቶችና ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አንጻር ያለውን ክፍተት በሙላት የሴቶችን እኩል መብትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ተጽእኖ ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች ላይ የሴቶች ተሳትፎና የአመራር ሰጪነት ሚና መጠናከር እንዳለበት ጠቅሰው ሁሉ ዐቀፍ መረጃና በቂ እውቀት ለሴቶች ተደራሽ ማድረግም እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡
በስብሰባው ከተለያዩ የዓለም አገራት የተወጣጡ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች በአካል እና በቪዲዮ ኮንፍረንስ እየተሳተፉ እንደሆነ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።