የአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽነር የነበሩት ምትኩ ካሳ በቁጥጥር ስር ዋሉ

ሐምሌ 6/2014 (ዋልታ) የአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት ምትኩ ካሳ በቁጥጥር ስር ዋሉ።

ኮሚሽነሩ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ነው ዛሬ በፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉት።

በፌደራል ፖሊስ በወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው ለኢቲቪ እንደገለጹት ኮሚሽነሩ በቁጥጥር ስር የዋሉት ኤልሻዳይ ከተሰኘ በጎ አድራጎት ማኅበር ባለቤት ጋር በመመሳጠር የሙስና ወንጅል ፈፅመዋል በሚል በመጠርጠራቸው ነው።

ይህ ኤልሻዳይ የተሰኘ ድርጅት በአዋሽ፣ በአዳማ፣ በሀዋሳ፣ በእንጅባራ በመሳሰሉ አካባቢዎች ተፈናቃዮች በሌሉበት ተፈናቃዮች አሉ በማለት በተደጋጋሚ ጊዜ የእርዳታ እህልና አልባሳት በመረከብ ሽጦ ለተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት መግዛቱ በምርምራ መረጋገጡን ነው ረዳት ኮሚሽነር ታደሰ የተናገሩት።

ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ ሰፊ ክትትል ሲያደርግ እንደነበረም ረዳት ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።