የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወጎኖች ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የሰብዓዊ ድጋፍ አደረገ

ሐምሌ 18/2016 (አዲስ ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ ኬቾ ቀበሌ ለደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወጎኖች ግምታቸው 45 ነጥብ 5 ሚሊዮን የገንዘብ፣ የህክምና ግብዓቶችና የአስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ቦታው መላኩን አስታወቁ።

በድጋፉ ሽኝት ሥነ ስርዓት ላይ ለወገን ቀድሞ መድረስ ቀዳሚ ተግባራችን ነው ያሉት ከንቲባዋ በከተማው ህዝብና አስተዳደር ስም ከጎናቸው መሆናችንን ለመግለፅ የከተማው አመራሮችን ወደ ቦታው በአካል መሄዳቸውን ገልጸዋል።

የጉዳቱን ልክ በቦታው በአካል በማየት ድጋፉን ለመቀጠል እንሰራለን ሲሉም አብሮነታቸውን ተናግረዋል።

ከተላኩት የድጋፍ አይነቶቹ ውስጥ አንቡላንስ፣ የህፃናት አልሚ ምግቦች፣ የአስቸኳይ ጊዜ ህክምና እርዳታ መስጫ መሣሪያዎች፣ መድኃኒቶች፣ እንሶላዎች፣ በርድልብሶች ሲሆኑ በገንዘብ 25 ሚሊየን እና በቁሳቁስ ደግሞ 20 ሚሊዮን ግምት እንዳላቸው የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።