የአዲስ አበባ ፖሊስ ለአፋር ክልል ከ4.1 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ

መጋቢት 18/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ለአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከ4 ሚሊዮን 189 ሺሕ ብር በላይ የሚገመት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አደረገ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እና የወደሙ ፖሊስ ጣቢያዎችን ለማቋቋም የሚረዳ በጥሬ ገንዘብ 400 ሺሕ ብር፣ የፅዳት እቃዎች፣ ልዩ ልዩ የታሸጉ ምግቦች፣ ኮምፒውተሮች፣ ፎቶ ኮፒ ማሽኖች፣ ሼልፍ፣ ወንበሮች እና ልዩ ልዩ ቁሳቁስ ነው በድጋፍ ያበረከተው፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል አለዲን አለሳ የአዲስ አበባ ፖሊስን ጨምሮ መላው የፀጥታ አካላት ከዋና ተልዕኳቸው ባሻገር በመሰል ሀገራዊ ጥሪ ወቅት ካላቸው ላይ ቀንሰው ለወገኖቻቸው ድጋፍ ማድረጋቸው ሕዝባዊነታቸውን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ አመራሮችና አባላት ላደረጉት ድጋፍ በአፋር ሕዝብና መንግሥት ስም ምስጋናቸው ማቅረባቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡
በአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀልና ትራፍክ አደጋ መከላከል ዘርፍ ም/ኮሚሽነር መንገሻ ሞላ በርክክቡ ወቅት የአፋር ሕዝብ ከጀግናው የአገር መከላከያ ጋር በመሆን የአገሩን ሉአላዊነት ለማስከበር እየከፈለ ያለው መስዋዕትነት የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ አመራሮችና አባላት “ለወገን ደራሽ ወገን ነው፤ በጀግንነት እንጠብቃለን ሕዝባዊ ወገንተኝነታችንን በድጋፋችን እናረጋግጣለን” በሚል መርህ ድጋፉን ማድረጋቸውን አስታውቀው ወደፊትም ችግሩን ለመፍታት በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡