የአዲስ አበባ ፖሊስ ፖሊሳዊ የደንብ ልብስና ዓርማ መቀየሩን ምክንያት በማድረግ የማብሰሪያ መርሀ-ግብር አዘጋጀ

ሰኔ 11/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ፖሊስ  ፖሊሳዊ የደንብ ልብስና ዓርማ መቀየሩን ምክንያት በማድረግ የማብሰሪያ መርሀ-ግብር በመስቀል አደባባይ ሊያካሂድ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ይህን ተከትሎ በዕለቱ ልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች የሚከናወኑ በመሆኑ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ 6 ሰዓት ድረስ የተወሰኑ መንገዶች ለትራፊክ ዝግ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡

በዚህም መሰረት ከኡራኤል ወደ መስቀል አደባባይ፣ ከኦሎምፒያ ወደ መስቀል አደባባይ፣ ከ4ኛ ክፍለ ጦር/ጥላሁን አደባባይ ወደ መስቀል አደባባይ ፣ከሀራምቤ ሆቴል ወደ መስቀል አደባባይ፣ ከለገሃር ወደ መስቀል አደባባይ፣ ከብሔራዊ ቤተ መንግስት ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስዱና በተጠቀሱት አካባቢዎች የሚገኙ መጋቢ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

አሽከርካሪዎችም አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረቡን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡