የአዳማ ከተማ አስተዳደር ለ340 የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ምትክ መሬት አስረከበ

ታኅሣሥ 20/2014 (ዋልታ) የአዳማ ከተማ አስተዳደር በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና በመንገድ ግንባታ ምክንያት መሬታቸው የተወሰደባቸውን አርሶ አደሮች በመለየት በቦኩ ሸነን ቀበሌ ምትክ መሬት አስረክቧል።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ኃይሉ ጀልዱ በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት አርሶ አደሩ በደላላ እንዳይበላ መሬቱን ጠብቆ እንዲያቆይ እና ተጠቃሚ እንዲሆን ክትትል ይደረጋል።

በኦሮሚያ ክልል ትልቁ የሪፎርም ሥራ የአርሶ አደሩን ህይወት መቀየር ላይ ያተኮረ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በአዳማ ከተማ አስተዳደር 34 አርሶ አደሮች መሃል ከተማ ላይ መሬት ወስደው ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ መደረጉን ከንቲባው አስታውሰዋል።

ከአርሶ አደሩ መሬቱን መውሰድ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊውን ካሳ መክፈልም እንደሚገባ ተወስኗል ያሉት ከንቲባው ከዚህ በፊት በካሬ 90 ሳንቲም ድረስ በአነስተኛ ዋጋ ለአርሶ አደር ካሳ ይሰጥ እንደነበርም አውስተዋል፡፡

አሁን ላይ ማሳውን ለአስፈላጊ ልማት የሚሰጥ አርሶ አደር እንደ አዳማ ከተማ 213 ብር በካሬ ሜትር ካሳ እንደምታሰብለትና በዚህም አርሶ አደሩ ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገባ እድል የሚከፍት ገንዘብ እንዲያገኝ የሚያስችል ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።

ካርታቸውን የተረከቡት 340 የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች በአባዎራ 500 ካሬ ሜትር ለልጆች ደግሞ ከ105 እስከ 200 ካሬ ሜትር መሃል ከተማ ላይ እንዲወስዱ የተደረጉ መሆናቸው ታውቋል።