የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ለማከናወን በሶስት ክልሎች ኮሚሽነሮች  ተሰማሩ

ሐምሌ 10/2016 (አዲስ ዋልታ) በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሀረሪ ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ለማከናወን ኮሚሽነሮች ማሰማራቱን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።

በ10 ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራን ለመከወን ዝግጅቱን   የጨረሰው ኮሚሽኑ የክረምቱ ወቅት እክል በማይፈጥርባቸው አካባቢዎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትን ጀምሯል።

አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራዎችን እስከ ነሀሴ 30/2016 ዓ.ም ድረስ ለማጠናቀቅ ያቀደው ኮሚሽኑ በአፋር ክልል የአካባቢው የሙቀት ሁኔታ ምቹ በሚሆንበት የጥቅምት ወር አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራውን ለመስራት እንዳቀደ ገልጿል።

በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ደግሞ አስቻይ ሁኔታ ሲፈጠር ሥራውን ለመስራት ዝግጁ እንደሆነም የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ገልጸዋል፡፡

ከግንቦት 21 እስከ 27/2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተደርጎ ከነበረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ የተወሰዱ ተሞክሮዎችን ወደ ክልሎች ለማስፋት ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።

ሁሉንም አካታች እንዲሆን የሚጠበቀው ብሔራዊ ምክክሩ የትኛውም ሀሳብ ካላቸው አካላት ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ያነሱት ዋና ኮሚሽነሩ ከ50 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብረው እየሰሩ እንደሆነ ገልጸው።

አብረውት ለማይሰሩ ፓርቲዎች እና በትጥቅ ትግል ላይ ላሉ አካላትም ጥሪ አቅርበዋል።

በአማረ ደገፋው