የአፄ ቴዎድሮስ ቁንዳላ ለሕዝብ እይታ ሊቀርብ ነው

ታኅሣሥ 16/2014 (ዋልታ) የጎንደር ከተማን ቱሪዝም ለማነቃቃትና የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር በጥምቀት በዓል የአፄ ቴዎድሮስ ቁንዳላን ለሕዝብ እይታ ሊቀርብ ነው።
የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዘውዱ ማለደ ከ150 ዓመታት የእንግዚዝ ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው የአፄ ቴዎድሮስ ቁንዳላ (ሹሩባ) ለሕዝብ ክፍት ይደረጋል ብለዋል።
ለዲያስፖራው የቀረበውን የወደ ሀገር ቤት ጥሪ ተከትሎ የጥምቀትን በዓል ለማክበር ወደ ከተማው የሚመጡ እንግዶች በሚስተናገዱበት ሁኔታ በጎንደር ከሆቴል ባለቤቶች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
የቱሪዝም እንቅስቃሴውንና የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር የአፄ ቴዎድሮስ ቁንዳላ በበዓሉ ወደ ከተማው መጥቶ በአገር ውስጥና በውጭ ቱሪስቶች እንዲጎበኝ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ቁንዳላው ከበዓሉ ቀደም ብሎ ወደ ከተማው የሚገባበት የክብር አቀባበል ሥነ ሥርዓት እንደሚከናወን ገልፀው ይህም ”ትልቅ የአገር ቅርስና ታላቅ ኩነት ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ጣሂር መሐመድ በበኩላቸው በክልሉ የገናና የጥምቀት በዓላትን በላሊበላና በጎንደር ከተሞች በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።