የአፍሪካ ልማት ባንክ በግብርና ቴክኖሎጂ አቅርቦት በኢትዮጵያ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ገለፀ

ሰኔ 18/2014 (ዋልታ) የግብርና ቴክኖሎጂ አቅርቦትን የሚደግፈው የአፍሪካ ልማት ባንክ መርኃ ግብር በኢትዮጵያ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ እያገዘ መሆኑን የባንኩ ፕሬዚዳንት ገለፁ።
ፕሬዚዳንቱ አኪንውሚ አዴሲና በቡድን ሰባት አገራት ስብሰባ ላይ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት በሩሲያና ዩክሬን ግጭት ምክንያት ብዙ አገራት ለምግብ ዋስትና ችግር ተጋልጠዋል ብለዋል፡፡
በዚህም 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ሕዝብ ያላት አፍሪካ የገፈቱ ቀማሽ መሆኗን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ አሁን ላይ ለአፍሪካ የምግብ እርዳታ መስጠት ላይ ሳይሆን ትኩረት ማድረግ ያለብን ምርታማነት ማሳደግ ላይ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
አፍሪካ በአሀኑ ሰዓት በቋቷ እንዲኖር የምትፈልገው የምግብ እህል ሳይሆን ምርጥ ዘር ነው ብለዋል፡፡
የአፍሪካ አርሶ አደሮች አስፈላጊው ቴክኖሎጂ ቢቀርብላቸው አፍሪካን መመገብ ይችላሉ ያሉት ፕሬዚዳንቱ ቴክኖሎጂ ለአፍሪካ ግብርና ሽግግር በተሰኘው መርኃ ግብር በሁለት አመት ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል ምርጥ ዘር ለ12 ሚሊየን የአፍሪካ አርሶ አደሮች እንደቀረበ ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለአርሶ አደሩ ሙቀትን መቋቋም የሚችል የስንዴ ምርጥ ዘር ድጋፍ በመደረጉ በሁለት አመታት ውስጥ 675 ሺሕ ሄክታር መሬት ማልማት የተቻለ ሲሆን ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርትንም በ80 በመቶ እንዲቀንስ ማስቻሉን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡
በባንኩ ለኢትዮጵያ በሚያደርገው ድጋፍ በሚቀጥለው ዓመት ከ1 ነጥብ 2 እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የሚደርስ ስንዴ ለኬንያና ጅቡቲ ለመላክ ማቀዱን ነው የተናገሩት።
የሩሲያና ዩኩሬን ግጭት በምግብ ዋስትና ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመመከት የአፍሪካ ልማት ባንክ ለአስቸኳይ የምግብ ምርት አቅርቦት የሚውል 1 ነጥብ 6 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ማፅደቁን ተናግረዋል፡፡
የአስቸኳይ የምግብ ምርት አቅርቦት እቅዱም ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በጥምረት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡