የአፍሪካ ልማት ፈንድ ለታዳሽ ኃይል ማስፋፊያ 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አጸደቀ

ሚያዝያ 3/2014 (ዋልታ) የአፍሪካ ልማት ፈንድ የዳይሬክተሮች ቦርድ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአራት ሀገራት ለታዳሽ ኃይል ማስፋፊያ 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አጸደቀ፡፡

ቦርዱ ድጋፉን ያጸደቀው በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ጂቡቲ እና ሱዳን በረሃማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ነው ተብሏል።

ድጋፉ በሀገራቱ በረሃማ አካባቢዎች የታዳሽ ኃይል ለማምረት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ የተደረገ መሆኑን ቦርዱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

አሁን የተደረገው ድጋፍ የአፍሪካ ልማት ፈንድ ለሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ ከሚደግፋቸው 15 ፕሮጀክቶች አንዱ ሲሆን ለሀገራቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ እንዲሆን በፀሐይ ኃይል የሚመረት ኃይል ፓርክ ጥናትን፣ ሀገራቱን በኃይል የሚያስተሳስር የኃይል ቋት ግንባታን፣ ከፍተኛ ኃይል የሚሸከም ገመድ ዝርጋታን ያካተተ መሆኑ ተመላክቷል።

ድጋፉ በቀጣናው የታዳሽ ኃይል ማበልጸግ ላይ የሚስተዋለውን ክፍተት የሚሞላ ከመሆኑም በተጨማሪ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰትን ችግር ለመቀነስ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW